1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባህል ዲፕሎማሲና የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ በበርሊን

ሐሙስ፣ መጋቢት 12 2016

በአብዛኛዉ አፍሪቃ ዉስጥ የመደማመጥ እ ና ችግርን በንግግር የመፍታት ባህል እንደሚያንሰን፤ ሕግ ኖሮን፤ አብዛኛዉን ጊዜ ተግባራዊ እንደማናደርግ፤ እንዲሁም ራስን ለመቻል ከመጣር ይልቅ እርዳታ መጠበቃችን፤ ይህ ደግሞ ዉጭ ከሚኖረዉ ዜጋ ጭምር መሆኑን ነዉ። በበርሊኑ የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ ፕሮፌሰር ዘነበ ከተናገሩት የተወሰደ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4dzXU
የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ 2024 በበርሊን
የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ 2024 በበርሊንምስል Academy for Cultural Diplomacy

የባህል ዲፕሎማሲ እና የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ በበርሊን 2024

«በአብዛኛዉ አፍሪቃ ዉስጥ የመደማመጥ እና ችግርን በንግግር የመፍታት ባህል እንደሚያንሰን፤ ሕግ ኖሮን ያወጣነዉን ሕግ አብዛኛዉን ጊዜ ተግባራዊ እንደማናደርግ፤ እንዲሁም ራስን ለመቻል ከመጣር ይልቅ እርዳታ መጠበቃችን፤ ይህ ደግሞ ዉጭ ከሚኖረዉ ዜጋ ጭምር መሆኑን በጉባኤዉ ላይ ካነሳሁት ነጥቦች መካከል ይገኙበታል።»

የባህል ዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል (ሲሲዲኤስ) በርሊን ላይ በአዘጋጀዉ ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የነበሩት በሩስያ ሞስኮ የአፍሪቃዉያን ዲያስፖራ አንድነት ፕሪዚደንት እና በሩስያ የሚኖሩ የኢትዮጵያዉያን ዋና ተጠሪ ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ ናቸዉ።  መዲና በርሊን ላይ የሚገኘዉ የባህል ዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል ባለፈዉ ሳምንት በአካሄደዉ የአዉሮጳ አፍሪቃ የባህል ልዉዉጥ መድረክ የአራት ቀናት ጉባዔ ላይ የአፍሪቃ ሃገራትን ልማት እና የባህል ልዉዉጡን ይበልጥ ለማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች ተወያይቷል ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበዉ ነበር። መቀመጫዉን በርሊን ላይ ያደረገዉ የባህል ዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል መስራች እና ዋና አስተዳዳሪ ማርክ ዶን ፍሪድ ድርጅታቸዉ በባህል ዲፕሎማሲ ጥናት ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በልማት ፕሮግራም ላይ ጉባኤ ማካሄዱን ተናግረዋል።  

የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ 2024 በበርሊን
የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ 2024 በበርሊንምስል Academy for Cultural Diplomacy

ባለፉት አስርት ዓመታት እየዳበረና እየተሻሻለ የመጣዉ የአዉሮጳ እና የአፍሪቃ ሃገራት ግንኙነት ሁለቱም አህጉራት በራሳቸዉ ብሎም በጋራ ለሚያደርጉት ልዩ ልዩ ተግባራት ስኬታማነት ወሳኝ ነገር እየሆነ መምጣቱን ድርጅቱ ይገልፃል። በባህል ዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል ለአራት ቀናት የተካሄደዉ ጉባኤ በመአከሉ እና በሌሎች ታዋቂ ድርጅቶች ብሎም በዲፕሎማቶች እና ምሁራን የተዘጋጀ መድረክ ነዉ። ጉባኤዉ በተለይ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ምጣኔ ሐብት፣ በሠላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ መብቶች፣ በኪነ-ጥበብና ባህል ዘርፎች ላይ የተለያዩ ክንዉኖች እና ጥናቶች የሚቀርቡበት ነዉ። በሞስኮ ነዋሪ የሆኑት እና ወደ አስራ ሁለት ሰዓታት ተጉዘዉ በርሊን በተዘጋጀዉ ጉባኤ ላይ የጥናት ጽሁፋቸዉን ያቀረቡት፤ በሞስኮ የአፍሪቃዉያን ዲያስፖራ አንድነት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያዉያን ተጠሪ ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ እንደነገሩን  ባለፉት በርካታ ዓመታት በርሊን በሚገኘዉ የባህል ዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል  እየተጋበዙ ይመጡ እንደነበር እና አሁንም በግብዣ መምጣታቸዉን ነግረዉናል።

የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ 2024 በበርሊን
የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ 2024 በበርሊንምስል Academy for Cultural Diplomacy

የባህል ዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል የተለያዩ የትምህርት እድሎችን በመስጠት ቀዳሚዉ ማዕከል መሆኑ ይታወቃል። በኦንላይን ማለትም በኢንተርኔት የትምህርት አሰጣጥ ዘርፍን ጨምሮ የባህል ጥናት ዲፕሎማሲ ማዕከሉ አጫጭር ስልጠናዎችም ይሰጣል። በርሊን ላይ በተዘጋጀዉ ጉባኤ ጀርመናዉያንን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ሃገራት የመጡ የዘርፉ ባለሞያዎች ታዋቂ ሰዎች እና ምሁራን እንደተገኙ የነገሩን ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ፤ ድርጅቱ አዘጋጅቶት የነበረዉ የባህል ልዉዉጥ ጉባኤ መድረክ እና በትይዩ የተዘጋጀዉ የኢኮኖሚ ጉባኤ መድረክ፤ በዝግጅቱ መጨረሻ እለት ሁለቱ መድረክ ወደ አንድ መድረክ መጥቶ ጉባኤዉ መጠናቀቁን ተናግረዋል። ፕሮፌሰር ዘነበ፤ የመጀመርያዉ የኤኮኖሚ ጉባኤ ሁለተኛዉ እና ፕሮፌሰር ዘነበ የተሳተፉበት የአፍሪቃ እድገት ጉባኤ 2024 የሚል እንደነበር ተናግረዋል። በተለያዩ ሃገራት የሚሰሩ ፊልሞች፤ ሥነ ጥበብ፤ ሥነ ጽሑፎች  በሃገራት መካከል ድልድይን በመገንባት የባህል ዲፕሎማሲ ለማስፋፋት ፤ ዴሞክራሲን ለማሻሻል ያላቸዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ። በበርሊኑ መድረክ ላይ የተገኙት አምባሳደሮች የባህልን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን  ስለወቅታዊ የአገራቸዉ ጉዳይ ማንሳታቸዉን ፕሮፊሰር ዘነበ ተናግረዋል። እንደ ፕሮፌሰሩ የአፍሪቃ ሃገራት ልዩ ልዩ ባህልና ኪነ-ጥበብ ብሎም ቋንቋ በዓለም መድረክ ምን ያህል ተጽኖ እያሳደረ እንደመጣ ያየሁበትም ነዉ ብለዋል። 

«የባህል ብቻ ሳይሆን አብዛኛዉ ንግግር ካደረጉት መካከል አብዛኞቹ አምባሳደሮች፤ ስለአገራቸዉ ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ነዉ የሰጡት። ለምሳሌ የኢራቅ አምባሳደር ነበሩ፤ የኒጀር፤ የኢኳተራል ጊኒ፤ የአንጎላ አምባሳደር፤ ዓለም አቀፍ ምሑራን፤   እንዲሁም እኔ ነዉ የተገኘነዉ። እኔ ያቀረብኩት በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ጀምሮ እስካሁንዋ ሩስያ ድረስ ስለሚገኙት አፍሪቃዉያን ነዉ። የአፍሪቃ ታሪክ የሚጀምረዉ አብርሃm ጋኒባል ከሚባለዉ ነዉ። ከዝያም ከትዉልዶች በኋላ አሌክሳንደር ፑሽኪን ይመጣል። በሶቭየት ህብረት ወቅት ብዙ ተማሪዎች ከተለያዩ አፍሪቃ ሃገራት ይመጡ ነበር። አሁን ግን እነዛ ተማሪዎች አብዛኞቹ ወደ ሌላ ሃገራት ሄደዋል። ከሶቭየት ህብረስ መፍረስ በኃላ ሩስያ እና ከሶቭየት ህብረት የተገነጠሉት ሃገራት ለአፍሪካዉያን የዜግነት መታወቅያ ሰጥተዋል። አሁን በሩስያ ዉስጥ 10ሺህ የሚሆኑ አፍሪቃዉያን ይኖራሉ። ከዝያ መካከል 120 ዉ ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ። በሩስያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ አፍሪቃዉያን የሚገኙት ናይጀርያዉያን ናቸዉ። የናይጀርያ ዜጎች አግብተዉ ወልደዉ ይኖራሉ። አብዛኞቹ የሚሰሩት በቋንቋ አስተማሪነት ነዉ በህጻናት መዋያ ወይም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት።

በሁለተኛ ደረጃ በርካታ የኮንጎ ዜጎች በሩስያ ይኖራሉ። አብዛኞቹ እንዲሁ የቋንቋ አስተማሪዎች ናቸዉ ጥቂት የሚባሉ ናይጀርያዉያን እና የኮንጎ ዜጎች፤ ደግሞ በህክምናዉ ዘርፍ ተሰማርተዉ ይኖራሉ። የአፍሪቃዉያን ልጆች የመጀመርያ ትዉልድ እንዲሁም ሁለተኛ ትዉልድ፤ ትምህርቱን ተምሮ ሃገሪቱን እየለቀቀ ወጥቷል። ኢትዮጵያዉያኑም እንዲሁ አብዛኞቹ ወጥተዉ ጥቂት ናቸዉ አሁን ያሉት።»  ትዉልዴ አሜሪካን ማሳቹሴትስ ነዉ ያሉን እና ከ20 ዓመታት በላይ በበርሊን ነዋሪ የሆኑት የባህል ዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል የድርጅቱ መስራችእና ዋና ተጠሪ ማርክ ዶንፍሪድ የጉባዬዉ ትኩረት የነበረዉ በአጠቃላይ የባህል ዲፕሎማሲ ላይ ያጠነጠነ ነበር።  

የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ 2024 በበርሊን
የአፍሪቃ የልማት ጉባኤ 2024 በበርሊንምስል Academy for Cultural Diplomacy

«የጉባኤዉ ትኩረት በአጠቃላይ በባህል ዲፕሎማሲ ላይ ያጠነጠነ ነበር። በባህል ዲፕሎማሲ  ሃገራት ግንኙነታቸዉን እንዴት ማጠናከር ይችላሉ? በሰዎች፤ በማህበረሰቦች እና በሃገራት መካከል በባህል ልዉዉጥ እንዴት ድልድይን መገንባት እንችላለን ስንል ነዉ የተወያየነዉ። በባህል ልዉዉጥ፤ የትምህርት ግንባታን፤ በማስረጽ ፤ መተማመንን በመወያየት እንዴት ልናመጣ እንችላለን የሚለዉን ነጥቦችንም አንስተናል። ይህ አይነቱን ዉይይት አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ላይ ከኢትዮጵያ ሚኒስትር መስርያ ቤት እና ከአፍሪቃ ህብረት ጋር በርካታ ዉይይቶችን አካሂደናል።» 

የባህል ዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል (ሲሲዲኤስ)ባዘጋጀዉ ጉባy ላይ የተሳተፉትን ፕሮፊሰር ዘነበ ክንፉ ታፈሰ እና የድርጅቱ ዋና ተጠሪ ማርክ ዶንፍሪድ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን፤ ሙሉ ስርጭቱን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።     

 

አዜብ ታደሰ 

ታምራት ዲንሳ