1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፤ የሥነ-ጥበብ ዲፕሎማሲ

ሐሙስ፣ የካቲት 21 2016

«ስለ ሥነ-ጥበብ ካወራን ፤ ወደ ሰላም ወደ ፍቅር ወደ አንድነት የሚልከን ጎዳ ነዉ። በአሁን ወቅት በተለያዩ ጉዳዮች የተወጠረ ዓለም ላይ ነዉ የምንገኘዉ። ይህን በሥነ-ጥበብ በኪነ-ጥበብ ማስተንፈስ ያስፈልጋል። በጎ ነገራችንን ማሰብ አለብን። በዓዉደ ርዕዩ ላይ የቀረቡት ስዕሎች ላይ እንደተመለከተዉ፤

https://p.dw.com/p/4czzw
አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ካሳ፤ የቤልጂየም ሉክዘምበርግ ኔዘርላንድ እና የአዉሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን
አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ካሳ በኤንባሲያቸዉ ለአዉሮጳ ዲፕሎማቶች ስለዓዉደርእዩ ሲያስረዱ ምስል Ethiopian Embassy to Belgium

ብረስልስ ኢትዮጵያ ኤንባሲ የተከፈተዉ የስዕል ዓዉደርዕይ በአይነቱ የመጀመርያ ነዉ

«ስለ ሥነ-ጥበብ ካወራን ፤ ወደ ሰላም ወደ ፍቅር ወደ አንድነት የሚልከን ጎዳ ነዉ። በአሁን ወቅት በተለያዩ ጉዳዮች የተወጠረ ዓለም ላይ ነዉ የምንገኘዉ። ይህን በሥነ-ጥበብ በኪነ-ጥበብ ማስተንፈስ ያስፈልጋል። በጎ ነገራችንን ማሰብ አለብን። በዓዉደ ርዕዩ ላይ የቀረቡት ስዕሎች ላይ እንደተመለከተዉ፤ ገጠሪትዋ ኢትዮጵያ ምን አይነት የአኗኗር ዘይቤ አላት፤ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶቻችን እንዴት አይነት ናቸዉ፤ ምንድን ነዉ ትርጉማቸዉ የሚለዉን መልስ የሚሰጥ ነዉ»    

በብረስልስ የሚገኙት የቤልጂየም ሉክዘምበርግ ኔዘርላንድ እና የአዉሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ካሳ በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ በኤምባሲዉ ዉስጥ ስለተከፈተዉ የሥዕል ዓዉደ ርዕይ ለዶቼ ቬለ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ ነዉ።

ብራስልስ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የአለ የሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ት/ቤት እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የሥዕል ዓዉደርዕይ ለተመልካቾች ይፋ አድርጓል። ዓዉደ ርዕዩ «ኢትዮጵያ የፍጥረት እና የሥልጣኔ መነሻ» "Ethiopia Land of Origins and Civilization" በሚል የተዘጋጀዉ ነዉ።

ብረስልስ ኢትዮጵያ ኤምባሲ የተከፈተዉ ዓዉደርዕይ በተለይ  የገጠሪቷ ኢትዮጵያን ውበት ፤ ከአክሱማውያን ስልጣኔዎች ጀምሮ እስከ ሐረር ዘመን የሚዘልቅ ጥንታዊ ታሪክ፣ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሳይንስ እና ሥነ ፈለክ በድንቅ የሥነ ጥበብ ስራዎች የተቀመጡበት እና ለተመልካቾች የቀረቡት ነበር። በዓዉደርዕዩ መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የአውሮጳ ህብረት የውጭ ግንኙነት ቢሮ ዋና ጸሐፊ ስቴፋኖ ሳኒኖ፤ የቤልጂየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ አምባሳደር ባርት ዴ ግሩፍ ፤ በቤልጅየም የውጭ ጉዳያ ሚኒስተር የሳህል አክባቢ ልዩ መልዕክተኛ፤  ዶ/ር ኖርበርት ሪቻርድ ኢብራሂም ተገኝተዋል። በተጨማሪም በብራሰልስ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የንግድ ተቋማት፣ ዩኒቨርስቲዎች እና ሚዲያዎች፣ በብራሰልስ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላትም ተካፋይ ነበሩ።  

በመክፈቻ ስነ-ሥርዓቱ ላይ አምባስደር ሂሩት ዘመነ፤  ኢትዮጵያ በዋናነት በአፍሪቃ የተተከለች፣ በዓለም ዙሪያ የተዘረጋች ሥር መሆኗን፤ ይህም ከጥንታዊ የአውሮጳ ከተሞች ጋር ከምታደርገው ግንኙነት ጀምሮ እስከ ሩቅ ምስራቅ ድረስ ይካሄድ የነበረ የረጅም ጊዜ የንግድ ግንኙነት እንደነበር ገልፀዋል። በረጅም ጊዜ ዓለምአቀፍ ግንኙነቷ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስከ አፍሪቃ ህብረት ከተለያዩ የዓለም ሀገራትም ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት የዘለቀ የብዙ ዓመት  ታሪክ ያላት አገር መሆኗን አንስተዋል። ኢትዮጵያ ከቤልጅየም ጋር የ118 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ከአውሮጳ ህብረት ጋርም ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀ ግንኙነት እንዳላት አምባሳደርዋ ተናግረዋል።  በአሁኑ ወቅት ዓለም ከዚህ በፊት ታይተው በማይታወቁ መጠነ ሰፊ ፈተናዎች እንደተደቀኑባት እና ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ፤ ሁሉም አገራት የባህል እሴቶቻቸውን ተጠቅመው፤ መስራት እንደሚኖርባቸው፤ ብሎም  ለመጪው ትውልድ የተመቻቸና ሰብዓዊ ዓለም ትቶ ለማለፍ  መትጋት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። በአዉሮጳ አካባቢ የምድረ ቀደምትዋ ኢትዮጵያን ገጽታን ለመገንባት ስራ ላይ መሆናቸዉን አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ከዶቼ ቬሌ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልፀዋል።

 

አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ካሳ፤ የቤልጂየም ሉክዘምበርግ ኔዘርላንድ እና የአዉሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን
አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ካሳ በኤንባሲያቸዉ ከአዉሮጳ ዲፕሎማቶች ጋርምስል Ethiopian Embassy to Belgium

በብረስልስ በሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለተመልካች ክፍት በሆነዉ የስዕል አዉደ ርዕይ ላይ ወደ 21 የሚጠጉ ታሪክና ባህልን የሚያንፀባርቁ ሥዕሎች ከአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የመጡ ናቸዉ። የሥነ- ጥበብ ት/ቤቱ ዳይሬክተር አቶ አገኘሁ አዳነም በዚህ ዝግጅት ላይ ተካፋይ ናቸዉ። የሥዕል ስራዎቹ፤ በተለይ ጥንታዊነታችንን ያጎሉ መሆናቸዉን የገለፁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ አገኘሁ አዳነ፤ በትርዒቱ ላይ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠርን፤ የሥነ ፈለክ ጥበብን፤ በአሳሳል ረገድም ጥንታዊ መሰረት ያላቸዉ ስዕሎች ፤ በትርዒቱ ላይ መቅረባቸዉን ተናግረዋል። ለምሳሌ የአክሱም ዘመን የድንጋይ ላይ ጽሑፎች፤ የአክሱም ዘመን የመገበያያ ሳንቲሞች፤ በዛግዌ ዘመን የነበሩ ከፍተኛ የግንባታ ጥበቦች፤ ሐረርን ስልጣኔ እና ዘመናዊነትን የሚያንፀባርቁ ፤ የተጋድሎ ታሪካችንንም የሚዘክሩ የሥነ-ጥበብ ሥራዎች በትርዒቱ ላይ መቅረባቸዉን አቶ አገኘሁ አዳነ ተናግረዋል። እነዚህ ስዕሎች የሃገርን የየእለት ትልልቅ ኹነቶችን በማሳየት አገርን ማስተዋወቅ እና አገርን መስበክ አገርን ወደፊት የማምጣት ዓላማ እንዳላቸዉ አቶ አገኘዉ አዳነ ተናግረዋል። ሥነ ጥበብ በዲፕሎማሲዉ ረገድ በዝምታ አገር እያስተዋወቀ ማህበረሰብን የሚቀራረብ ጉልበት እንዳለዉም ተናግረዋል።

አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ካሳ፤ የቤልጂየም ሉክዘምበርግ ኔዘርላንድ እና የአዉሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን
አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ካሳ በአዉሮጳ ከሚገኙ ዲፕሎማቶች ጋርምስል Ethiopian Embassy to Belgium

 

«ሥነ ጥበብ የአንድን አገር ልዕልና ታላቅነት፤ የመንፈስ ብርታት ፤ የስልጣኔ ልክ በዝምታ የሚሰብክ ኃይል ማለት ነዉ። ከዚህ አንጻር ሥነጥበብን በተመለከተ የሚደረጉ ዝግጅቶች ከፍተኛ ጉልበት አላቸዉ። በስብሰባ በመግለጫ የማይሰማ መልክት በሥነ-ጥበብ የፈለጉትን ሃሳብ በሰዉ ላይ ማስረፅ ይቻላል። ሥነ ጥበብ በፍላጎት የሚዝናኑበት እና የሚማሩበት የሞያ ዘርፍ ነዉ።  በብራስልስ እየተካሄደ ያለዉ የሥነ-ጥበብ ዓዉደርዕይ ጥሩ ጅማሮ እና በተለያዩ የሞያ ዘርፎች መቀጠል ያለበት ተግባር ነዉ» 

እስካሁን እንዳየነዉ ወደ አዉሮጳ ባህላዊ የኪነ-ጥበብ ቡድን ይመጣል ፤ ከፍሎ ለሚገባ ወይም ለተመረጠ ተመልካች አሳይቶ ይሄዳል በአገራት መካከል በሚደረግ ግንኙነትም  በስብሰባ ተቀምጦ ንግግር ማድረግ ሳይሆን ወይም እስከዛሬ ይታይ ከነበረዉ አይነት ግንኙነት ወጣ ባለ መልኩ ነዉ አሁን ይህ የሥነ-ጥበብ ብሎም የባህላዊ ዲፕሎማሲ ግንኙነት የታየዉ እና ፋይዳዉም ትልቅ ይመስላል። 

አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ካሳ፤ የቤልጂየም ሉክዘምበርግ ኔዘርላንድ እና የአዉሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን
አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ካሳ፤ የቤልጂየም ሉክዘምበርግ ኔዘርላንድ እና የአዉሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን ምስል Ethiopian Embassy to Belgium

በብራስልስ ቤልጂየም ኢትዮጵያ ኤምባሲ የተከፈተዉ የሥዕል ትርዒት  ላይ የቀረቡት አንዳንዶቹ ሥዕሎች እድሜያቸዉ ወደ 100 ዓመት የሚጠጋ እና  በአለ የሥነ-ጥበብ ት/ቤት በቅርስነት ተጠብቀው የቆዩ መሆናቸዉ  ተመልክቷል። ዛሬ የሚጠቃለለዉ ይህ የሥዕል ዓዉደርዕይ በምሳሌነት በሌሎች የአዉሮጳ ብሎም የዓለም ሃገራት ዉስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ መጠርያ ተቋማት ላይ ቀጣይነት ቢኖራቸዉ የኢትዮጵያን ገጽታ ከመገንባቱ ረገድ ብሎም በሃገራት መካከል ባህላዊ ትስስርን በማጠናከሩ ረገድ ፍይዳዉ ትልቅ ይመስለናል። ቃለ ምልልስ የሰጡንን በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ