1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፍልሰትአፍሪቃ

አስከፊዉን የስደት ጉዞን የሚተርከዉ ስደተኛዉ ጋዜጠኛ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 29 2016

ከ 97 ምርጫ በኋላ በኢትዮጵያ ለስደት ከተዳረጉት ከ 108 በላይ ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ አንዱ ነዉ። ሱዳን ያገኛቸዉ ኢትዮጵያዉያን መሰሎቹ ገሚሱ ሱዳን በረሃ፤አልያም ሊቢያ በረሃ ህይወታቸዉ አልፋል። በረሃዉን ያለፈ፤ በደላሎች ተዘርፈዋል። ከዚህ ሲያልፍ ጋዜጠናዉ እንደሚለዉ በሜዲተረንያን የዉኃ መቃብር ተዉጧል»

https://p.dw.com/p/4Yd8t
ሎዛ - ዘ-ጸአት፤ የኢትዮጵያዉያን የአስከፊዉ የስደት ጉዞን የሚተርከዉ መጽሐፍ
ሎዛ ዘ-ጸአት ምስል Merid Estifanos

ሎዛ - ዘ-ጸአት የኢትዮጵያዉያን የስደት እንግልት እዉነተኛ ታሪክ

«የመላኩ ቤት ሁሉም ኢትዮጵያዎ አለበት። አማራ፤ ኦሮሞ ትግሬ፤ ወላይታ፤ አርጎባ፤  ጉራጌ። በሃይማኖቱም ቢሆን ኦርቶዶክሱም ፤ ፕሮቴስታንቱም፤ ሙስሊሙም አለ። እነዚህ ልዩነቶች ግን ፈጽሞ አይስተዋሉም። ካርቱም ሁለተኛ ቀን ሆነኝ። ነጋ፤ ያዉም ዛሬ ሙቀት ነዉ። ገና በጠዋቱ ሁሉ ነገር ወደ ትኩሳት ተቀይሯል። ከመላኩ በስተቀር ሁሉም እቤት ዉስጥ አሉ። ጠዋት እንደተነሳን መዝሙር ተከፈተ። የፕሮቴስታንት መዝሙር ነበር። የዘማሪዉን ማንነት ባላዉቀዉም፤ “ተሻገር ያለዉ ሂድ  እለፍ ያለዉ ፤ ጌታ ታማኝ ነዉ” ይላል መዝሙሩ። ሁሉም ዘምሩ የተባሉ ይመስላu። እየተሳሳቁ እየተቀላለዱ ይዘምራሉ። መሐመድ አጎርቤም ይዘምራል። የሥራ ድርሻ ያላቸዉም ፤ ዉጭ የነበሩ ፍራሾችን ከፊሎቹ ይሰበስባሉ፤ ዉስጥ ያሉት ደግሞ ቤት ያፀዳዳሉ። ከፊሎቹ ደግሞ የሚታጠቡ ልብሶች እና እቃዎች ላይ አተኩረዋል። የቤቱ ታናሽ መጣና እዉስጥ እያነጠፍ ን ነዉ ትገባለህ? አሁን ግን የሚታጠብ ልብስ ካለህ እንድትሰጠኝ ነዉ። »

  የባሻ አሸብር የጀርመን ተሞክሮ

በጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ የተደረሰዉ እና በእዉነተኛ ታሪክ ላይ ከተመሰረተዉ ሎዛ - ዘ-ጸአት ከተሰኘዉ  ድርሰት ላይ የተወሰደ ትረካን ነበር ያደመጥነዉ።  ጤና ይስጥልኝ አድማጮች እንደምን አመሻችሁ። ጋዜጠኛዉ የሜዲተራንያን ባህርን፤ የባህር ላዩ መካነ መቃብር ይለዋል። ህይወት አንዳንዴ ለመኖር የሚያስፈልግህን ያህል አትሰጥህም ሲል ስደተኛዉ ጋዜጠኛ መርዕድ ይናገራል ። ለመኖር የሚያስፈልግህ አስራ አምስት ብር ቢሆን፤ ህይወት አምስትዋን ትሰጥሃለች። ቀሪዋን አስር ብር ፍለጋ ትወጣለህ። ታገኛታለህ ወይ አታገኛትም። የሰዉ ልጅ በጦርነት ምክንያት እራሱን ወይም ቤተሰቡን ለማትረፍ ይሰደዳል ። ፀጥታና ሰላምን ያገኛታል ወይ አያገኛትም። የሰማይ ዉኃ ይነጥፍ እና መሪትም የወይን ፍሪዋን መስጠትዋን ታቆም እና ገበሪዉም ሞፈሩን ሰቅሎ ዉኃ ወዳለበት ይሰደዳል። በማህበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ፍትህ በማጣት የሰዉ ልጅ ለስደት ይዳረጋል። ስደት በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የሰዉ ልጅ ታሪክ ነዉ። እነሆ የሎዛ - ዘ-ጸአት ስደተኞች በአንድ ምክንያት ተሰደዋል። ሁሉም ፀሎታቸዉ አንድ አይነት ነዉ። ሁሉም ለፈጣርያቸዉ ስለት እያደረጉ ነዉ። ሁሉም ከተለያየ የህይወት ቋት የተተፉ ናቸዉ። አለሙበት ደርሰዋል አልያም በዉቅያኖሱ ተዉጠዋል በአጋቾች ታርደዋል፤ በደፋሪዎች እንዳይሆን ሆነዋል። ስደተኞቹ ጥቁርም ነጭም፤ የቀይ ዳማም ናቸዉ ። የቀለም ልዩነት ግን አያዩም። የተለያዩ ቋንቋን ይናገሩ እንጂ ዘር የሚቆጥሩም አይደሉም፤ ሃይማኖት የላቸዉም፤ ይለናል ደራሲ እና ጋዜጠኛ፤ መርዕድ እስጢፋኖስ። ይህን የፈጠረዉ የፍላጎታችን አንድ መሆን ነዉ? ወይስ የብዙዎቻችን ተመሳሳይነት ወይስ ሁለቱም እያልኩ በስደት ዉስጥ ያሉ የህይወት ተሞክሮዎችን ፤ ከርቀት ለማየት ሞከርኩ ።  

ጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ፤ ሎዛ - ዘ-ጸአት ደራሲ
ጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ፤ ሎዛ - ዘ-ጸአት ደራሲ ምስል Merid Estifanos

«እዚህ ቤት ዉስጥ አንድ አይነት አየር ይጠቀማል። እርግጥ ነዉ እንዱ ወደ ዉስጥ አየር ሲምግ አንዱ ደግሞ ወደ ዉጭ በመተንፈስ አየር ያስወጣል። በልዩነት ብዙ ሆኖ እንደ አንድ መኖር መቻል፤ እንዴት አይነት አስደሳች መስተጋብር ነዉ?» ሲል ጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ ይናገራል።

ከሩዋንዳዉ አስከፊ ታሪክ ምን እንማር?

የራሱን እና ሌሎች ወጣት ኢትዮጵያዉያን የስደት እንግልት ህይወትን በብዕሩ ያሰፈረዉ ደራሲ እና ጋዜጠና መርዕድ እስጢፋኖስ፤ በኢህአዴግ መንግሥት በተለያዩ የነጻዉ ፕሬስ ጋዜጦች ላይ በዋና አዘጋጅነት እና በከፍተኛ ሪፖርተርነት አገልግሏል።  ከዚህም ጋር በተያያዘ በቀድሞ መንግሥት አምስት ጊዜ ታስሯል። ምርጫ 1997 ን  ተከትሎም ታስሯል። ቆየት ብሎ በሽብር እና ህገ-መንግሥትን በመናድ ተጨማሪ ክስ ከቀረበበት በኋላ ግን አገር ለመሰደድ ወስኖ ከአገር ወጣ። ዛሬ ጋዜጠኛዉ የሚኖረዉ ፈረንሳይ ፓሪስ ላይ ነዉ። ሃገር ቤት ሳለ ከርቸሌ ዘብጥያ ከወረደ እና በዋስ ከተፈታ በኋላ፤ ለህይወቴ አሳሳቢ በመሆኑ ለመሰደድ ወሰንኩ፤ ከኔዉ ጋር በዝያን ወቅት ከ 108 በላይ ጋዜጠኞች ተሰደዋል ሲል በሁመራ በኩል በሱዳን የስደት ይህ ህይወትን መቀላቀሉን ነግሮናል።  ታዋቂዉ የጥበብ ሰው ሃብታሙ ማሞ  

ጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ፤ በሁመራ በኩል ሱዳን ገብቶ፤ የመኖርያ ፈቃድ ስለሌለዉ በአጋጣሚ የሱዳን ኃይላት ይዘዉት ለጥቂት ጊዜያት ሱዳን ዉስጥ ታስሯል። ይሁንና በጋዜጠኝነቱ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት ያዉቀዉ ስለነበር፤ ድርጅቱ ተከራክሮ ከእስር አስፈታዉ። ከዝያም በሱዳን ሰባት ወር ከ 23 ቀናት ቆይቼ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪዉ ድርጅት ወደ ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ወሰደኝ ብሎናል። 

ፓሪስ ከተማ
ፓሪስ ከተማ ምስል Shotshop/IMAGO

ጋዜጠኛ መርዕድ ሎዛ - ዘ-ጸአት በተሰኘዉ መጽሐፉ የስደትን አስከፊነትን ይሁን በጎ ገጽታን አሳይቼበታለሁ  ብሎ ያምናል። በወቅቱ በኢትዮጵያ በነበረዉ ፖለቲካ ተከሰዉ ለስደት ከተዳረጉት ከ108 በላይ ጋዜጠኞች መካከል እሱ እራሱም አንዱ ነበር።  ሱዳን የተዋወቃቸዉ የስደት ጓዶቹ፤ ገሚሱ ሱዳን በረሃ አልያም ሊቢያ በረሃ ህይወቱ አይፏል። በረሃዉን ያለፈ፤ ሊቢያ በረሃ ላይ ወድቋል፤ አልያም በህገወጥ ሰዎችን በሚያዘዋዉሩ ሰዎች ተዘርፈዋል። ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ፤ ጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ እንደሚለዉ« በሜዲተረንያን ባህር ማለትም በባህር መቃብር ተዉጠዉ ቀርተዋል።»

´´የከተማው መናኝ´´ ኤልያስ መልካ ሕይወት

ጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ በሱዳን በኖረባቸዉ ወራቶች በሱዳኖች ቀናነት፤ ለርዳታ ዝግጁነት፤ እና ይቅርባይነት እጅጉን ተማርኳል። ደራሲዉ በመጽሐፉ የአብዛኛዉን ኢትዮጵያዊ ባህሪ ከሱዳናዉያን በማነጻፀር ተችቷል። መነገር ያለበት በግልፅ ሊነገር ይገባል የሚል አቋምም አለዉ።    

ጋዜጠኛ መርዕድ እስጢፋኖስ በቅርቡ የአዉሮጳ የስደት ኑሮና የኢትዮጵያዉያንን ኑሮ የሚያሳየዉን ሁለተኛ መጽሐፉን ለአንባቢ ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቆ ጨርሷል። ጋዜጠኛዉን በድጋሚ ይዘን እንቀርባለን። በዚህ ዝግጅት ለሰጠን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ