1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዞሊንገኑ የቀኝ ጽንፈኞች ጥቃት 30ኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 29 2015

በቤቱ ውስጥ ተኝተው የነበሩ ሦስት ልጃገረዶችና ሁለት አዋቂ ሴቶች ተገደሉ።ጥቃቱ በመላ ጀርመን የሚገኙ ቱርካውያንን አመጽ የተቀላቀለበት ተቃውሞ አስነሳ።ድርጊቱን የተቃወሙት ቱርኮች ብቻ አልነበሩም።በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ጀርመናውያንና ሌሎችም ጭምር እንጂ።የሟቾቹ ቤተሰቦች በግፍ የተገደሉት እነዚህ ቱርኮች እንዳይረሱ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ።

https://p.dw.com/p/4SGvC
Deutschland Solingen Brandanschlag 30. Jahrestag Gedenkfeier
ምስል David Young/dpa/picture alliance

የቀኝ ጽንፈኞች ጥቃት 30ኛ ዓመት

ቱርኮች በጥላቻ የተገደሉበት የዞሊንገን ጀርመኑ የቀኝ ጽንፈኞች ጥቃት 30ኛ ዓመት ባለፈው ሳምንት ታስቧል።  ዞሊንገን ራድዮ ጣቢያችን በሚገኝበት በኖርድ ራይን ቬስትፋለን ፌደራዊ ግዛት ውስጥ የምትገኝ ከተማ ናት። ከፌደራል ግዛቱ ዋና ከተማ ዱስልዶርፍ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ዞሊንገን ለረዥም ጊዜ ሻምላ ቢላዋ መቀስና ምላጭ በሚያመርቱ ስም ባላቸው በተለያዩ ኩባንያዎች ትታወቅም ነበር። ከዛሬ 30 ዓመት ወዲህ ግን የዚህች ከተማ መታወቂያ ሌላ ሆኗል። ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን ከተዋሀዱ ከሁለት ዓመት በከተማይቱ ቀኝ ጽንፈኞች በቱርኮች ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ ግድያ ታዋቂ አድርጓታል። ወቅቱ አንድ የሆነችው ጀርመን በቀኝ ጽንፈኞች የተጥለቀለቀችበት ጊዜ ነበር።በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤትም ፖለቲከኞች በሀገሪቱ እየጨመረ በመጣው የስደተኞች ቁጥር ምክንያት ተገን አሰጣጡ እንዲገደብ ይከራከሩ ነበር።በጎዳናዎች ላይ ሳይቀረ ዘረኛ ጥቃቶች መድረስ ጀመሩ፤ አንዳንዴም ሰዎች ይገደሉ ነበር።በተለይ በምሥራቅ ጀርመኖቹ ሆየርስቬርዳ እና ሮስቶክ ሊሽተንሀገን ከተሞች በሰሜን ጀርመኑ በመለን ከተማ እንዲሁም በዞሊንገን በስደተኞች መኖሪያዎች ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች ይጠቀሳሉ።ከመካከላቸው አምስት ወጣት ልጃገረዶች እና ሴቶች በቁማቸው ተቃጥለው የተገደሉበት የዞሊንገኑ ጥቃት እነሆ ባለፈው ሳምንት 30ኛ ዓመቱ ታስቧል። በዞሊንገኑ የመታሰቢያ ስነስርዓት ላይ የጀርመን መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሟቾች ቤተሰቦችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል። 
የዶቼቬለው ፔተር ሄለ እንደዘገበው ጥቃቱ በተፈጸመበት ቤት አቅራቢያ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የተተከሉት ዛፎች አሁን ቁመታቸው በአደጋው እንዳልነበረ ከሆነው ቤት ጋር ይስተካከላል።ዛፎቹ ፈክተዋል፤ቤቱ ግን ዳዋ ለብሷል።ሰው ይኖርበት እንደነበረ የሚያስታውሱ አንዳንድ ምልክቶች አሁንም አሉ።የሟቾቹ ቤተሰቦች በግፍ የተገደሉት እነዚህ ቱርኮች እንዳይረሱ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ።በቀኝ ጽንፈኞች በተቀነባበረው በዚህ ጥቃት የቺሀት ጌንሽ ሁለት እህቶች ተገድለዋል። ሁሊያና ሴይም ይባላሉ።የዘጠኝኝ እና የአራት ዓመት ልጆች ነበሩ። ከነርሱ አጠገብ ጉርሱን ኢንስሀቲሽ ጌንሽ እና ግጉሊስታን ኦዝቱርክ ሕይወታቸው አልፏል። እነዚህን የቀኝ ጽንፈኞች ሰለባዎች ማሰብ ዘረኝነትን ለመዋጋት ለሚደረገው ትግል ወሳኝ ነው ይላል የ26 ዓመቱ ጂሀት ጌንሽ። ጌንሽ እንደሚለው በዚህተግባር ደግሞ ሁሉም ሊሳተፍ ይገባል።
«ይህ የማኅበረሰቡ ጉዳይ ነው። ሁሉም ተሳታፊ ሊሆን ይገባል።እንደ ወላጅ፣እንደ መምህር፣እንደ ስራ ባልደረባ እና ወዳጆች የሚገባንን ድርሻ መወጣት አለብን፤ስለ ወንጀሉም መናገር አለብን። 
የዞሊንገኑ ጥቃት በዘመናዊት ጀርመን ታሪክ እጅግ አሰቃቂ ከሚባሉት ጥቃቶች አንዱ ሲሆን በጀርመን የውጭ ዜጎችን በመጥላት የሚፈጸም ጥቃት ማሳያም ሆኗል። በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 28 ለግንቦት 29 አጥቢያ 1993 የዛሬ 30 ዓመት ነበር አራት እድሜያቸው ከ16 እስከ 23 የሚደርስ ከአፍቃሪ ናዚዎች ጋር ግንኙነት ያለው የቀኝ ጽንፈኛ ቡድን አባላት ይህን ጥቃት ያደረሱት።አራቱ ወጣት ወንድ ጀርመናውያን በዞሊንገን ከተማ በአንድ የቱርክ ተወላጆች ቤተሰብ ቤት ዙሪያ ቤንዚን አርከፍክፈው እሳት ለኮሱበት።  በቤቱ ውስጥ ተኝተው የነበሩ ሦስት ልጃገረዶች እና ሁለት አዋቂ ሴቶች ተገደሉ። አደጋው በመላ ጀርመን የሚገኙ ቱርካውያንን አመጽ ለተቀላቀለበት ተቃውሞ አስነሳ። ድርጊቱን የተቃወሙት ቱርኮች ብቻ አልነበሩም።በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ጀርመናውያንና ሌሎችንም ጭምር እንጂ። ድርጊቱን የተቃወሙ የተሳተፉባቸው ትላልቅ ሰልፎችም ተካሄዱ። አሰቃቂው ወንጀል ከተፈጸመ ከሁለት ዓመት በኋላ ጥቃት አድራሾቹ የእሳት አደጋ በማድረስ እና በግድያ ጥፋተኛ ተብለው ከ10 እስከ 15 ዓመት የሚደርስ እሥር ተፈረደባቸው። ለደረሰው ግድያና ጥፋት ተጠያቂ የተባሉት ፍርዳቸውን አጠናቀው ነጻ ከእስር ከተፈቱ ብዙ ጊዜያት አልፈዋል። የ30ኛው ዓመት መታሰቢያ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ከመካከላቸው ሦስቱ በጠበቃቸው አማካይነት ባስተላለፉት መግለጫ እኛ ከደሙ ንጹህ ነን ብለዋል። ጂሃት ጌንሽ ጥቃት አድራሽ ተብለው ከተፈረደባቸው በኋላ ፍርዳቸውን ጨርሰው ከእስር የተለቀቁት ስለላኩት መልዕክት አስተያየት መስጠት አልፈለገም።ስለ ወንጀለኞቹ ግን ምን ይሰማው ይሆን?ጥላቻ ወይስ ሌላ ? 
«ጥቃት አድራሾቹ ቢያንስ ቢያንስ እንደ እኔ ወላጆች እንዲሰቃዩ እፈልጋለሁ። ሆኖም ጥላቻ የለኝም ሃይማኖቴም አይፈቅድልኝም። በተቻለኝ መጠን ጥላቻዬን ለማሳነስ እሞክራለሁ።»

Deutschland Gedanken an Familie Genc
ምስል Tuncay Yildirim/DW
Brandanschlag Solingen 1993
ምስል Rene Tillmann/IMAGO

የዞሊንገን ከተማ በአያቱ በሜቭሉድ ጌንሽ ስም አደባባይ ለመሰየም ወስኗል። በዚህ ደስተኛ ነው። አያቱ ሁለት ሴቶች ልጆች ሁለት የልጅ ልጆች እንዲሁም አንድ የእህት ወይም የወንድም ልጅ ሞተውባቸዋል። በ2022 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት እርቅ እንዲወርድ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበሩ የሰላም አምባሳደር ሆነው ነበር። እስከ ዕለተ  ሞታቸው ድረስ የተለያዩ ባህሎች በመከባበር አብረው እንዲዘልቁ ዘመቻ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ወደፊት በስማቸው ይሰየማል የተባለው አደባባይ በመሀል ዞሊንገን በርካታ እንቅስቃሴ ባለበት መንገድና በመኖሪያ ቤቶች መሀል ነው የሚገኘው። የልጅ ልጃቸው ጂሀት ብዙ ጊዜ ወደ አደባባዩ አይሄድም ። ቤተሰቡ የሚፈልገው በአያቱ ስም መንገድ እንጂ አደባባይ እንዲሰየም አይደለም።
«በርግጥ እና እንደ ቤተሰብ በሜልቩደ ጌንሽ ስም መንገድ እንዲሰየም ነው የምንፈልገው። ለጊዜው ግን አደባባዩን በርሷ ስም በመሰየሙ ረክተናል። ግን ለጊዜው ብቻ ነው።»
ጌንሽ እንደሚለው ምኞታቸውን ለማሳካት በጥረታቸው ይገፋሉ። 
ከአደባባዩ ብዙም ሳይርቅ ሴቲንና አጋሮቹ በተለይ መሠረታቸው የውጭ ለሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ያስጠናሉ። በክፍሉ ግድግዳ ላይ የአንድ በሁሉም ትምሕርት በጣም ጥሩ ውጤት ያገኘ ተማሪ ሰርተፊኬት ተለጥፏል። ይህ ሌሎችን ለማነቃቃት ታስቦ የተደረገ ነው። ከዚህ ሌላ ሴቲን በከተማዋ ምክር ቤት በዋነኛነት መሠረታቸው የውጭ የሆነ ሰዎችን ስጋቶችን የሚያሳውቀው እንቅስቃሴ ሊቀ መንበርም ነው። ዞሊንገን 160 ሺህ ነዋሪዎች አሏት። ከነዋሪዎቿ ከሦስቱ አንዱ አንዱ የውጭ ዜጋ መሠረት ያለው ነው።ከ30 ዓመት በፊት እነዚህ ሰዎች በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ፈጽሞ የሉም። ሁላችንም የኅብረተሰቡ አካል ነን የሚለው ሴቲን ከኢጣልያ ከስጳኝ እና ከቱርክ እንግዳ ሠራተኞች ጀርመን ከመጡ 60 ዓመት እንደሆናቸው ያስታውሳል። ዘረኝነትንም በጋራ ልንዋጋው ብቻ የምንችል በሽታ ነው ይላል። 
በአሁኑ ጊዜ በጀርመን ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ቱርኮች ይኖራሉ። የዛሬ ሰላሳ ዓመት በዞሊንገን ጥቃት ሲደርስ ብዙዎች ፍርሀት አድሮባቸው ነበር። መሰረታቸው የቱርክ የሆነ በርካታ የጀርመን ነዋሪዎች ምናልባትም የምንኖርበት ህንጻ ቢያቃጥሉብን ሕይወታችንን ለማትረፍ ይረዳናል በሚል የገመድ መሰላሎች ገዝተው ያስቀምጡ ነበር።ዞሊንገን የተወለደው ኤርካን ሳሪካያ በዚያን ጊዜ የሆነውን በደንብ ያስታውሳል። ስለ ጥቃቱ የሰማው እግር ኳስ በመጫወት ላይ ሳለ ወንድሙ እየሮጠ መጥቶ ከነገረው በኋላ ነው።
«እሞታለሁ የሚል ፍርሀት ነበር መጀመሪያ የተሰማኝ። ከአንድ ሰዓት በኋላ አደጋ የሚደርስበት ቀጣዩ ቤት የኛ ይሆናል ከዚያ ደግሞ ይቀጥላልብለን ነበር የምናስበው።እውነት ለመናገር ይህን ነበር የምናስበው።»
ሳሪክያ ከጥቃቱ በኋላ የተነሳውን ተቃውሞም ያስታውሳል። በአሁኑ ጊዜ በዞሊንገን ውስጥ በአንድ ኩባንያ ውስጥ የሚሰራው ሳራክያ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት በከተማዋ ይህን መሰል ዘረኛ ጥቃት አጋጥሞም አላየሁም፤ ሰላማዊ ከተማም ነበረች ይላል። 
«እንዲህ ዓይነት ነገር ደርሶ አያውቅም። ሁሉ ነገር ጥሩ ነበር። ሁሉም ሰላማዊ ነበር። እስከዚያች ቀን ድረስ»
ሳሪካያ የእሳት ጥቃቱ ያስከተለውን ተቃውሞም ከዐዕምሮው አልጠፋም ። በወቅቱ በድርጊቱ የተቆጡ ቱርኮች እና ጀርመኖች በከተማዋ ማዕከል ድንጋይ በመወርወርና የሱቆችን መስኮቶች በመሰባበር ቁጣቸውን ይገልጹ እንደነበር ትዝ ይለዋል። ከዞሊንገኑ ጥቃት ወዲህ በጀርመን ቀኝ ጽንፈኞች በውጭ ዜጎች ላይ በሚያደርሱት ጥቃት የሚሞቱት ቁጥር እየቀነሰ ሄዷል። ስደተኞች ወደ ጀርመን በብዛት በገቡበት በ2015 እና በ2016 ግን ጥቃቱ ጨምሮ ነበር።  አማዱ አንቶንዮ የተባለው ድርጅት 161 ሰዎች በቀኝ ጽንፈኞች ጥቃት እንደሞቱ መዝግቧል። አሁን ዞሊንገን ሰላማዊ በመሆንዋ ሳሪካያ ደስተኛ ነው። የተወለደባትና  የሚሰራባትና አሁንም የሚኖርባት ዞሊንገን  እንደቀድሞ በሻምላ በቢላዋ እና በምላጭ ምርቶችዋ እንጂ የዛሬ ሰላሳ ዓመት በቱርኮች ላይ በደረሰው ጥቃት ብቻ እንድትታወስ አይፈልግም።

Deutschland Gedanken an Familie Genc
ምስል Tuncay Yildirim/DW
Mevlüde Genç
ምስል Bernd Thissen/dpa/picture alliance

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ