1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ ጉብኝት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 27 2015

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከባንኩ መሪ ጋር ትናንት እንደተነጋገሩ ገልፀው የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የትብብር አድማስ በማስፋት ለኢኮኖሚ እድገት ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አቅርቦት እና የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎችን የሚደግፍ የዘለቀ አስተዋፅዖ ይኖረዋል በማለት ጉብኝቱ መልካም ውጤት እንዳለው አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/4UeSx
Äthiopien Addis Abeba | Besuch Weltbank Präsident Ajay Banga
ምስል Solomon Muchie/DW

የዓለም ባንክና ኢትዮጵያ በቅርቡ የ400 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተፈራርመዋል

የዓለም ባንክ የፕሬዝደንትነትን ሥልጣን በቅርቡ የተረከቡት  ኦጃይ ባንጋ ከትናንት ጀምሮ ኢትዮጵያን እየጎበኙ ነዉ።ባንጋ እስካሁን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፣ ከገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ፣ ከልዩ ልዩ ፋብሪካዎች ባለቤቶች እና ሥራ ፈጣሪዎች ጋር መነጋገራቸዉን አስታዉቀዋል።በሚመሩት ባንክ ድጋፍ የተገነባውን አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘውን የቦሌ ለሚ 2 ኢንደስትሪ ፓርክን የሥራ እንቅስቃሴም  ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ጎብኝተዋል።የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ጉብኝት በኢትዮጵያዉ ጦርነት ምክንያት የሻከረዉን የኢትዮጵያንና የዓለም አበዳሪ ተቋማትን ግንኙነት ለማሻሻል ይረዳል ተብሎ ይገመታል።

 

ዛሬ የቦሌ ለሚ 2 ኢንደስትሪ ፓርክ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴን ከጎበኙ በኋላ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ተጨባጭ ሁኔታ ለመመልከት መምጣታቸውን የገለፁት የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት ከትናንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ያሉ ጥሩ ያሏቸውን የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን ገልፀዋል።

መንግሥት ለኢንዱስትሪ ማዕከሉ የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎችን እዚሁ ለማምረት እያደረገ ያለውን ጥረት በበጎ ያነሱት እኒሁ የገንዘብ ተቋም መሪ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለማስፋፋት፣ እሴት ጨምሮ ምርትን ወደ ውጪ ለመላክ የሚደረግ ያሉትን ጥረትም አድንቀዋል።

የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ኦጃይ ባንጋ የቦለ ለሚ 2 ኢንዱስትሪ ፓርክን ሲጎበኙ
የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ኦጃይ ባንጋ የቦለ ለሚ 2 ኢንዱስትሪ ፓርክን ሲጎበኙምስል Solomon Muchie/DW

 

"ዛሬ የተመለከትሁት ነገር በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ዘጠና በመቶ ይሆናሉ ልላቸው ለምችላቸው ለወጣቶች በተለይ ለሴቶች ሥራ የሚያስገኙ ፋብሪካዎችን እና ሥራን የሚፈጥሩ የኢንዲስትሪ መንደሮችን መፍጠር እና ያንን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት በሚያስችል እንዲሁም ወጣቶች ራሳቸውን እንዲችሉ በሚያደርግ ሁኔታ ማከናወን እጅግ በጣም ጥሩ ሥራ ነው። አለም ባንክ ከኢንደስትሪ ማዕከላት ጋር በመተሳሰሩ ደስተኛ ነው። በእርግጥም አለም ባንክ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ከጅቡቲ የሚያገናኘውንና ሥራ ፈጣሪዎች የወጪ እና ገቢ ምርት ፍሰት እንዲያሳድግላቸው የሚረዳቸውን ፈጣን መንገድ ለመገንባት የሚያስችለውን ገንዘብ በቅርቡ በመፈራረማቸውም ደስተኛ ነው" ብለዋል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከባንኩ መሪ ጋር ትናንት እንደተነጋገሩ ገልፀው የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የትብብር አድማስ በማስፋት ለኢኮኖሚ እድገት ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አቅርቦት እና የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎችን የሚደግፍ የዘለቀ አስተዋፅዖ ይኖረዋል በማለት ጉብኝቱ መልካም ውጤት እንዳለው አመልክተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የአለም ባንክ በማህበራዊ ልማት፣ በመሠረተ ልማት፣ በቀጣናዊ ትስስርም ሆነ በሌሎች ብዙ ዘርፎች ትልቁ የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ የልማት አጋር መሆኑን ዛሬ ቦሌ ለሚ ሁለትን ከእንግዳው ጋር ከጎበኙ በኋላ ተናግረዋል።

የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ኦጃይ ባንጋና ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ
የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ኦጃይ ባንጋና ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድምስል Solomon Muchie/DW

 

"የልማት ምንጮቻችንን በማስፈት ረገድ የግል ዘርፉን ሀብት በመሳብ ከአለም ባንክ ጋር እንሠራለን። በተለይም ኢትዮጵያ በአካባቢው በሰው ሀብት ብዛት የላቀ ቁጥር ያላት ሀገር እንደመሆኗ፣ ከብዙ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ድንበር የምትጋራ መሆኗ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደት እጅግ መሰረታዊ እና ጠቃሚ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ስለ ጉብኝት ታችሁ እጅግ በጣም እናመሰግናለን። ይህ የሦስት ቀናት ጉብኝት ከአለም ባንክ ጋር ያለንን ግንኙነት በላቀ ለማጠናከር ይረዳናል። ኢትዮጵያ በለውጥ እና በኢኮኖሚ እድገት ጉዞዋ ፣ በብሔራዊ አንድነት እና በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሥራዋ ጠንክራ ትቀጥላለች። በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአካባቢው የመረጋጋት እና የአንድነት መሪ ሆና እንድትቀጥልም እንሠራለን" ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ እና የአለም ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሚገኙ ሴቶችን እና ወጣቶችን በላቀ  ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ለታመናበት የትምህርት ጥራት ማሻሻያ እና የሥርዓተ ምግብ ማበልፀጊያ ተግባር የሚውል የተባለለትን የ400 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት በቅርቡ ተፈራርመዋል።

 

ሰሎሞን ሙጪ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ