1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ኢንደስትሪ ዞኖች እጣፈንታ እና የፖሊሲ ለውጥ

ሐሙስ፣ ግንቦት 8 2016

አንድ የኢኮኖሚ ተንታኝ እንደሚሉት የኢንደስትሪ ፓርኮችን ይተካል ተብሎ የተጀመረው የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታም የተያዘለትን ውጥን ከግብ ማድረሱ ቀላል የሚሆንለት አይመስልም፡፡ የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ የመጀመሪያው ግብ ምን ነበር?

https://p.dw.com/p/4fwgC
Äthiopien Addis Abeba 2024 | Rolle der Industriedörfer für die äthiopische Wirtschaft
ምስል Seyoum Getu/DW

የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ የመጀመሪያው ግብ ምን ነበር?

ባለፈው ዓርብ ግንቦት 02 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል በሞጆ ከተማ አቅራቢያ የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ ኢትዮጵያ ከኢንደስትሪ ፓርኮች ይልቅ ለኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታ በር የሚከፍት ፖሊሲ ማውጣቷን ጠቁመው ነበር፡፡

ይህ የመንግስት ውሳኔ ከዚህ በፊት በከፍተኛ የውጪ ብድር በብዛት የተገነቡትን  የኢንደስትሪ ፓርኮች ግብና ስኬታማነት ሊጎዳው እንደሚችል የሰጉ አሉ፡፡

አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ አንድ የኢኮኖሚ ተንታኝ እንደሚሉት የኢንደስትሪ ፓርኮችን ይተካል ተብሎ የተጀመረው የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታም የተያዘለትን ውጥን ከግብ ማድረሱ ቀላል የሚሆንለት አይመስልም፡፡

የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ የመጀመሪያው ግብ ምን ነበር?

የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ ከፍተኛ የውጪ ብድር ተመቻችቶላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት መሰራት ከጀመሩ ገና አስር ዓመታት ማስቆጠሩ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አምስት እና ስድስተኛ ዓመታቸው ላይ ናቸው፡፡ መቀመጫቸውን ለንደን ያደረጉት የኢኮኖሚ ተንታኙ አብዱልመናን መሃመድ የነዚህኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ዋና ግብ ይህ ነበር ይላሉ፡፡ "ዋና ዓላማው የነበረው የውጪ ንግድን ማበረታታት ነበር፡፡ የተለያዩ ማኑፋክቸሮች አንድ ቦታ መሰባሰባቸው እርሰበርስ እንዲመጋገቡና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር የመንግስት አገልግሎትንም ሰብሰብ አድርጎ መስጠትና መሰረተልማቶችን አንድ ላ በቀላሉ ማቅረብ የሚሉ ውጥኖችም ነበሩት፡፡ የውጪ አልሚዎች በተሻለ የውጪ ገቢያውን ውቁታል በሚል በብዛት እንዲገቡ” በሚል በስፋት እንዲሳተፉ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡

"የተጠበቀውን ግብ ያልመጣው” የኢንደስትሪ ዞኖች ግንባታ

ባለሞያው ብዙ የተጠበቀበት ኢንደስትሪ ዞኖች ግንባታ እና ስራው የተጠበቀውን ያህል ውጤት አላስገኘም ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የተወሰኑ ኢንቨስተሮች መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ ምክኒያቶችን አንስተዋል፡፡ "የውጪ ምንዛሪ እጥረት ያስከተለው የግብዓቶች አቅርቦት ችግር ኢንቨስተሮችን መፈተኑ፣ የመንግስት ቢሮክራሲ እና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአገር አለመረጋጋት፣ በኃል አቅርቦት መቆራረጥ ተፈላጊው ውጤት አልመጣም” ብለዋል የኢኮኖሚ ተንታኙ፡፡

"የኢንደስትሪ ዞኖችን ወደ ጎን ያለው” የፖሊሲ ለውጥ

ባለፈው ዓርብ በገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ስራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመሰል ፕሮጀክቶች ግንባታ በኢትዮጵያበስፋት ስገነባ ከነበረው የኢንደስትሪ ፓርኮች ላይ የፖሊሲ ለውጥ መደረጉን ጠቁመው ነበር፡፡ "የኢንደስትሪ ፓርኮችን በብድር እየገነባን ለውጪ ዜጎች ብቻ የተከለለ እያደረግን የኢትዮጵያን ኢንደስትሪ መለወጥ አንችልም፡፡ በፖሊሲ ለውጥ ያመጣንብት አንዱ ነገር የኢንደስትሪ ፓርኮችን በብድር ከመገንባት ነጻ የንግድ ቀጠናን ለግሉ ማህበረሰብ አስቻ ሁኔታ በመፍጠር የውጪና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ተጋግዘው ሳፋፊ ኢንደስትሪ የሚገነቡበት አውድ መፍጠር ነው” ብለዋል፡፡ ይህ የፖሊሲ ለውጥ ከተደረገ በኋላ በድሬዳዋ ከተመሰረተው ነጻ የንግድ ቀጠና ቀጥሎ ይህ በሞጆ እና አዳማ መካከል የሚገነባው የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በቀጣይነት የተጀመረው የንግድ ቀጠና ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ የመጀመሪያው ግብ ምን ነበር?
የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ የመጀመሪያው ግብ ምን ነበር?ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የፖሊሲ ለውጡ ተጽእኖ

የኢኮኖሚ ተንታኙ አብዱልመናን መሀመድ የፖሊሲ ለውጥን አስከትሏል የተባለው የኢንደስትሪ ዞኖች እምብዛም ስኬታማ አለመሆን በቀጣይ ኢትዮጵያ  ውስጥ በስፋት ይሰራበታል የተባለውን ነጻ ኢኮኖሚ ዞኖችስ ምን ያህል ግቡን እውን ያደርገዋል የሚለውን በጥያቄ ውስጥ ያስቀምጣሉ፡፡ "ያ ግቡን ባልመታበት እንደገና ተመሳሳይ ጽንሰሃሳብ ይዞ መምጣት ከኢኮኖሚ ይልቅ ፖለቲካ መስላል” ይላሉ፡፡ ባለሙያው አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጪ ባለሃብቶች በተጨማሪ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን በአዲሱ ፖሊስ ለመሳብ ሲያቅዱ ዋናው ኣላማ "የውጪ ንግድን ማበረታታት ወይስ ከውጪ የሚገባውን ምርት መተካት” የሚለው የበለተ ማብሪያ የሚፈልግ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የፖሊሲ ለውጡ ከፍተኛ የውጪ ብድር ወጥቶባቸው በስፋት የተገነቡትን የኢንደስትሪ ፓርኮች እጣፈንታ አደገኛ መስመር ውስጥ ሊያስገባ ይችላል ብለዋል፡፡ "የፖሊሲ ለውጡ ነባሩን የኢንደስትሪ ፓርኮች ትኩረት ስለሚቀንስ ቀስ በቀስ ኢንቨስተሮች እየለቀቁ የሚወቱ ከሆነ ከመዳከምም አልፎ ዳዋ ይበላቸዋል” ያሉት ባለሙያ ያ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ለአገር ኪሳራ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶትስ ስለሺ

ታምራት ዲንሳ