1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ታዬ ደንደዓ የፍርድ ቤት ውሎ

ሐሙስ፣ ግንቦት 1 2016

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ በቅርቡ ከጠበቆቻቸው ጋር ችሎት ከቀረቡ በኋላ የክስ ዝርዝር ደርሷቸው ክሱም በንባብ ከተሰማ በኋላ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው በጠበቆቻቸው ጥያቄ ቀርቦ ነበር።

https://p.dw.com/p/4fg3P
አቶ ታዬ ደንዳኣ። ፎቶ፦ ከማኅደር
የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንዳኣ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ብይን ለመስጠት ለግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ታዬ ደንደአ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤት ብይን ሰጥቷል፡፡ ዋስትና ላይ የግራ ቀኝ ክርክር መርምሮ ብይኑን የሰጠው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሕገመንግስትና ሕገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት አቶ ታዬ የዋስትና መብቱን የተከለከሉት የተከሰሱበት ተደራራቢ ክሶች ዋስትናን ስለሚያስከለክሉ ነው ብሏል፡፡

የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ በቅርቡ ከጠበቆቻቸው ጋር ችሎት ከቀረቡ በኋላ የክስ ዝርዝር ደርሷቸው ክሱም በንባብ ከተሰማ በኋላ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው በጠበቆቻቸው ጥያቄ ቀርቦ ነበር።

ዛሬ በዚሁ በአቶ ታዬ ጉዳይ ያስቻለው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለት ጉዳዮችን ለመመልከት እንደሆነም ከጠበቆቻቸው አንዱ አቶ ቱሊ ባይሳ ለዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ "አንደኛው በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ አቃቤ ሕግ በጽሑፍ አስተያየት እንዲሰጥበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያቀረብነው የዋስትና ትያቄ ላይ ችሎቱ ብይን እንዲሰጥ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱም የዋስትና መብቱን በተመለከተ የቀረበባቸው ክስ ተደራራቢ መሆኑንና ክሶቹ ከፍ ያለ ቅጣት የሚስቀጡ በመሆኑ የዋስትናው ጥያቄውን አልተቀበለም ፍርድ ቤት፡፡ በዚህም ደንበኛችን ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወርደው ከአቻዎቻቸው ጋር እንዲታሰሩ ችሎቱ በይኗል” ነው ያሉት፡፡ አቶ ቱሊ አቃቤህግ ያቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይም ፍርድ ቤት ብይን ለመስጠት ለግንቦት 13 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ቀጠሮ መያዙን አስረድተዋል፡፡

ስለቀረበውም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያም ዝርዝር ጉዳይ የተጠየቁት ጠበቃ ቱሊ ባይሳ፤ "አንደኛው ክሱ ወንጀል አይደለም  በወንጀልም አያስከስስም የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አንደኛ እና ሁለተኛ ክሶች በአንድ ላይ መጠቃለል የነበረባቸው እንዲሁም ሶስተኛው ክስ የአንቀጽ ስህተት ያለበት ነው” በሚል መቅረቡን አንስተዋል፡፡

በአቶ ታዬ ክስ ላይ ከዚህ በፊት ጠበቆች ደንበኛቸው በዋስ እንዳይለቀቁ የሚከለክል የህግ መሰረት የለም ብለው ስከራከሩ፤ ዐቃቤ ሕግ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሞ በሰበር ሰሚ ችሎት ዋስትናን በልዩ ሁኔታ ሊከለክል የሚችልባቸው ነጥቦችን ማለትም በተደራራቢ ክስ መከሰሳቸውንና የተከሰሱበት ድንጋጌ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስጥል ከሆነ ዋስትና ሊያስከለክል ይችላል በማለት ተከራክሮ ነበር።

አቶ ታዬ ደንዳኣ። ፎቶ፦ ከማኅደር
አቶ ታዬ ደንዳኣ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Million Haileselasi/DW

አቶ ታዬ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ላይ ዛሬ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ አስተያየቱን በጽሑፍ የሰጠ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱም የክስ መቃወሚያው ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ተገልጿል።

የፍትሕ ሚንስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ክሶችን ማቅረቡ ይታወሳል።

ይኸውም ክስ፥ ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሰላም ሚንስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስት እና የሕዝብን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው ከመንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ የገቡትን የ"ኦነግ ሸነ እና ፋኖ” ዓላማን ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፤ በስማቸው በተከፈተ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መሰል ይዘት ያለው መልእክቶችን አስተጋብተዋል የሚል ይገኝበታል፡፡

ሌላው የቀረበባቸው ክስ ተከሳሹ ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሣሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታኅሣሥ 1 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5:00 ሰዓት ላይ በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ከሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና ከ60 ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል የሚል ነው።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር