1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴኔጋል ተቃውሞ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ይጎዳ ይሆን?

ቅዳሜ፣ ሰኔ 3 2015

የሶንኮ ደጋፊዎች እንደሚሉት መሪያቸው ሶንኮ የተፈረደባቸው የፍትህ ስርዓቱ ባቀነባበረው ሴራ ነው። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ግን ይህን ያስተባብላሉ። ከዚህ ሌላ ሳል ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን ይወዳደሩ አይወዳደሩ ግልጽ ባለማድረጋቸው አለመረጋግት ፈጥሯል። ተችዎች እንደሚሉት ሳል እንደገና ለመወዳደር የሚዘጋጁ ከሆነ ሕገ መንግሥቱን ይጥሳሉ።

https://p.dw.com/p/4SPVQ
Senegal Dakar | Proteste zur Unterstützung des Oppositionsführers Sonko
ምስል Leo Correa/AP/dpa/picture alliance

የሴኔጋል ተቃውሞ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ይጎዳ ይሆን?

ባለፈው ሰሞን በሴኔጋል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ሊያናጋ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። ማንሶር ሳምቤ የተባሉ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ሀገሪቱ በቢሊዮኖች የሴኔጋል መገበያያ ገንዘብ ፍራንክ የሚቆጠር ገንዘብ በተቃውሞው ወቅት አጥታለች ይላሉ። ሆኖም ዶቼቬለ ያነጋገራቸው አዶልፎስ ምዋሎ ምንም እንኳን ግጭቱ የሴኔጋልን ገጽታ ቢያጠለሽም ኤኮኖሚው ላይ ግን ያን ያህል ጫና አይኖረውም ብለዋል። በርሳቸው እምነት መንግሥት ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ማዋል ይችላል። 
በጎርጎሮሳዊው 2024 በሴኔጋል በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚወዳደሩት ኡስማኔ ሶንኮ  ወጣቶችን በጥቅም በመደለል ተከሰው ከአንድ ሳምንት በፊት የሁለት ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል። ከዚህ ቀደም ከተመሰረተባቸው የአስገድዶ መድፈር ክስ ደግሞ ነጻ ተብለዋል። በሶንኮ ላይ የሁለት ዓመት እሥራት ከተበየነ በኋላ በሶንኮ ደጋፊዎችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ 16 ሰዎች ተገድለዋል። ግጭቱ ምዕራብ አፍሪቃዊቷን ሀገር ሴኔጋልን በአሥርት ዓመታት ውስጥ ካጋጠማት የከፋው ተብሏል።በተቃውሞ ወቅት የግልና የመንግሥት ድርጅቶች እንዲሁም ሱቆች ተዘርፈዋል። በወቅቱ የዩኒቨርስቲያዎች ህንጻዎች የነዳጅ ማደያዎች፣ ባንኮች የገበያ መደብሮችና የመንግሥት አስተዳደር ህንጻዎች እንዳልነበሩ ሆነዋል። በብጥብጡ ሰበብ በተለያየ ንግድ የተሰማሩ ሰዎች ብዙ ኪሳራ ደርሶብናል ይላሉ። እንደ 19 ዓመቱ ምጋየ ጋየ አይነቶቹ የሚመጣውን በመፍራት አስቀድመው ሱቃቸውን ዘግተዋል።በነዚህ ቀናት ታዲያ ምንም ዓይነት ገቢ አልነበራቸውም።ልብስ ሰፊው ሞዱሶንኮጉዬ ስራውን ባቆመበት ወቅት ለክፉ ጊዜ ያጠረቀመውን ገንዘብ በሙሉ ጨርሷል። ደንበኞቹ ፈርተው ወደ ርሱ ዝር አላሉም ነበርና።እናም ብዙ ቀናት ያለ ስራ አሳልፈዋል። 
«እነዚህ በእለት ተዕለት ኑሮአችን የሚገጥሙን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ናቸው።ያለ ስራ ቀናትን ማሳለፍ በጣም ከባድ ነው።ምክንያቱም ንግዳችን ባለበት እንደቆመ ነው። የሰዎች እንቅስቃሴ ተገድቧል። እንደ ከዚህ ቀደሙ በየዕለቱ የምናገኘው ገቢ የለንም። ሰልፉ ቆሞ ስራችንን ለመጀመር  ተስፋ እናደርጋለን። ስራችንን መከወን እንድንችል በእውነት ሁኔታዎች ወደ ቀድሞው እንዲመለሱ እፈልጋለሁ። »
የሶንኮ ደጋፊዎች እንደሚሉት መሪያቸው ሶንኮ የተፈረደባቸው የፍትህ ስርዓቱ ባቀነባበረው ሴራ ነው። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ግን ይህን ያስተባብላሉ። ከዚህ ሌላ ሳል ለሦስተኛ የስልጣን ዘመን ይወዳደሩ አይወዳደሩ ግልጽ ባለማድረጋቸው አለመረጋግት ፈጥሯል። ተችዎች እንደሚሉት ሳል እንደገና ለመወዳደር የሚዘጋጁ ከሆነ  ሕገ መንግሥቱን ይጥሳሉ። እናም ሶስት ታዋቂ የስነ ጽሁፍ ሰዎች ለዚህ መፍትሄው ሳል ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን አልወዳደርም ብለው በይፋ ማሳወቃቸው ነው ሲሉ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ አሳውቀዋል። ማኪ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ እወዳደራለሁ ካሉ ብዙዎች እንደሚሉት መጠነ ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ሊቀሰቀስ ይችላል። አመጹ ከቀጠለ ደግሞ በሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ሀገራት ላይም ከፍተኛ ችግር ማስከተሉ አይቀርም።ግጭቱን  በሽምግልና ለመፍታት ጥረት እንዲደረግም እየተጠየቀ ነው።  በርካታ ሴኔጋላውያን ግርግሩ እንዲቆም ይፈልጋሉ ሌሎች ደግሞ ሶንኮ ፍትህ እስኪያገኙ ድረስ ተቃውሞውን እንቀጥላለን ይላሉ ። 

9 killed in violent protests against opposition leader's sentencing in Senegal
ምስል Annika Hammerschlag/AA/picture alliance
Senegal Ziguinchor | Proteste zur Unterstützung des Oppositionsführers Sonko
ምስል Muhamadou Bittaye/AFP

ኂሩት መለሰ