1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩሲያ የዩክሬን ወረራና ያስከተለው ውግዘት

ሐሙስ፣ የካቲት 17 2014

ሩሲያ ክሬሚያን በኃይል ከዩክሬን ከገነጠለች ካለፉት ስምንት አመታት ወዲህ በሁለቱ ሀገሮች መካከል  ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።ከሰሞኑ ደግሞ ሩሲያ  ለሁለት የዩክሬን ግዛቶች የመገንጠል ዕውቅና በመስጠቷ ክሬንን እና አጋሮቿን አስቆጥቷል።

https://p.dw.com/p/47YAy
Ukraine Konflikt | Russischer Militärangriff
ምስል AP Photo/picture alliance

የሩሲያ የዩክሬን ወረራ እና ያስከተለው ውግዘት

 

በምስራቃዊ ዩክሬን  ዶንባስና ሉሃንስክ ለተባሉ  እና መገንጠል ለሚሹ  ሁለት ግዛቶች፤ ሩሲያ እውቅና መስጠቷን  እንዲሁም ወደ ግዛቶቹ «የሰላም አስከባሪ» በሚል ወታደሮቿን ማስገባቷን ተከትሎ፤በሁለቱ ሃገራት መካከል  ውጥረት ነግሶ ቆይቷል። በዛሬው ዕለት ደግሞ የሩሲያ ወታደሮች በተለያዩ አቅጣጫዎች የዩክሬን ድንበር አቋርጠው በክሬሚያ እና ሌሎች የሰሜን ዩክሬን ግዛቶች መግባታቸውን የሀገሪቱ የድበር ፀጥታ ሀይሎች ይፋ አድርገዋል።ይህ የሩሲያ ወረራ የሁለቱ ሀገሮች ውጥረት እንዲካረር ከማድረጉ ባሻገር፤ በሩሲያ ላይም ሰፊ  ውግዘት አስከትሏል።
ወረራውን ተከትሎ መጀመሪያ ውግዘት ያሰሙት  የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ  ሲሆኑ፤ሩሲያ በዩክሬን ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሟን ገልፀው ጥቃቱን ኮንነዋል።ፕሬዝዳንቱ የሀገሪቱ ዜጎች ቤታቸው እንዲቆዩ በማሳሰብ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ወታደራዊ ህግ  መደንገጋቸውንም አስታውቀዋል። 
የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት መግለጫ ተከትሎም  የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ላደረሰችው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት፤ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥል አስታውቋል። የውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ዴር ሌየንም ለጥቃቱ ሩሲያን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት ህብረቱ ከዩክሬንና ከህዝቦቿ ጎን እንደሚቆም አእስታውቀዋል።
«ዛሬ ማለዳ  የሩስያ ወታደሮች ነፃ እና ሉዓላዊት ሀገር  ዩክሬንን ወረዋል።እናም አሁን በአውሮፓ ንፁሀን ሴቶች፣ ወንዶች እና ህጻናት ህይወታቸውን አጥተዋል።ወይም ለህይወታቸው እየፈሩ ነው። ይህን አረመኔያዊ ጥቃት እና ጥፋቱን ፍትሃዊ ለማድረግ ሚሰነዝሩ ክርክሮችን እናወግዛለን። ጦርነትን ወደ አውሮፓ መልሰው ያመጡት ፕሬዝዳንት ፑቲን ናቸው። እናም በዚህ ጨለማ ሰዓት የአውሮፓ ህብረት  ከዩክሬን እና ከህዝቦቿ ጎን ይቆማል። »
በሌላ በኩል የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ምክንያታዊ ያልሆነ እና ያልተገባ ” ሲሉ የሩሲያን ጥቃት  ኮንነዋል።ፕሬዚዳንቱ በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥሉም ቃል ገብተዋል። የጀርመኑ መራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልስ በበኩላቸው "ሩሲያ በዩክሬን ላይ የሰነዘረችው ጥቃት በግልጽ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥስ እና ምንም አሳማኝ ምክንያት የሌለው ነው ብለዋል።ኦልፍ አያይዘውም፤ለዩክሬን አስከፊ ቀን፤ ለአውሮፓም ጨለማ ቀን ነው ብለዋል። 
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ፑቲን "የደም መፋሰስን መንገድ መርጠዋል" ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ በበኩላቸው ስለሰብዓዊነት ሲባል ፑቲን ወታደሮቻቸውን ከዩክሬን እንዲያስወጡ ተማፅነዋል።
«ፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን፤ በሰብዓዊነት ስም ወታደሮቸዎን ወደ ሩሲያ ይመልሱ።ስለ ስብዓዊነት ብለው  በክፍለ ዘመኑ  እጅግ የከፋ ሊሆን የሚችል ጦርነት በአውሮፓ እንዲጀመር አይፍቀዱ።." 
የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ይህ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለአውሮፓ በጣም ጨለማ ከሆኑት ጊዚያት ውስጥ አንዱ ነው” ብለዋል ።ቦሬል ፤ በሩሲያ ላይ አዲስ ጠንካራ  ማዕቀብ ለመጣል ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ለመስራት ቃል የገቡ ሲሆን፤ ሩሲያ  «ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ መገለል» እንደሚገጥማት  አስጠንቅቀዋል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ኔቶ ዛሬ ሐሙስ ካደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላም ሁለቱ ሀገራት በሚዋሰኑበት
ምሥራቃዊ ግዛት የምድር፣ የባህር እና የአየር ኃይሉን ለማጠናከር መወሰኑን አስታውቋል።
ይህንን ሁሉ  ልመና፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ከምንም ያልቆጠሩት የሩሲያው ፕሬዝደንት  ቭላድሚር ፑቲን ግን በሀገራቸው የቴሌቭዥን ጣቢያ ባደረጉት ንግግር፤ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ ሀገራትን ድርጊታችሁ "አይታችሁት የማታውቁትን ዳፋ ያስከትላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
«በእኛ ጣልቃ ሊገባ እና ከዚህም በላይ በሀገራችን እና በህዝባችን ላይ ስጋት ለመፍጠር ለሚሞክር የሩስያ ምላሽ ፈጣን ይሆናል። ይህም በታሪካችሁ አጋጥሟችሁ ወደ ማያውቅ  መዘዝ  እንደሚመራችሁ እወቁ።ለሚከሰተው ማንኛውም ነገር  ሁሉ ዝግጁ ነን። በዚህ ረገድ አስፈላጊ ውሳኔዎች ሁሉ ተደርገዋል። እንደምትሰሙኝ ተስፋ አደርጋለሁ።» 
ሩሲያ የዩክሬን አካል የነበረችውን ክሬሚያ የተባለች ቦታ በኃይል በመገንጠል የግዛቷ  አካል ያደረገችው በጎሮጎሪያኑ 2014 ዓ/ም ከስምንት አመታት በፊት ነበር። 

Russland Moskau | Vladimir Putin
ምስል Alexey Nikolsky/AFP
Ukraine Konflikt | Ukrainische Streitkräfte
ምስል Anatolii Stepanov/AFP/Getty Images
Ukraine Konflikt | Präsident Volodymyr Zelenskyy
ምስል Ukrainian Presidential Press Office/AP Photo/picture alliance

 

ፀሀይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ