1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፦ህዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2016

ያለስምምነት ያበቃው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነግ ኦነሠ) የሰላም ድርድር ፣የመንግሥታቱ ድርጅት በአማራ ክልል የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች አሳሰቡኝ ማለቱ እና የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ከእስራኤል ጋር የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሙሉ ማቋረጡ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ይቃኛል ።

https://p.dw.com/p/4ZNd9
Israel rescues some 200 citizens and Jews from Ethiopia conflict region
ምስል AP/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር / የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በምህጻሩ ኦነግ/ኦነሰ ሲል የሚጠራው ቡድን ሁለት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ  ዳሬሰላም ታንዛንያ ውስጥ ያካሄዱት የሰላም ንግግር ያለ ውጤት ማብቃቱን ሁለቱም ወገኖች በዚህ ሳምንት አጋማሽ ነበር ያሳወቁት። የኢትዮጵያ መንግሥት  ደርድሩ የከሸፈው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በድርድሩ “መንግሥት አዝሎ መንግሥት ያድርገኝ” ከሚል ያለፈ መደራደሪያ  ማምጣት ባለመቻሉ ነው ብሏል ።ኦነግ ኦነሰ በበኩሉ ድርድሩ ያለ ስምምነት ያበቃው የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱን የደኅንነት እና የፖለቲካ ፈተና ውስጥ ለከተቱ መሠረታዊ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት ባለማሳየቱ ነው ሲል ተችቷል። 
ባልሰመረው የመንግሥትና የኦነሠ ንግግር ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ጽንፍ የያዙትንና ዘለፋዎችን ያካተቱትን ወደ ጎን በመተው ሌሎቹን ስንመለከት የድርድሩን አስፈላጊነት ያነሱ፣ ቀድሞም ቢሆን በድርድሩ እምነት እንደሌላቸው የገለጹ ድርድሩ ባለመሳካቱ ያዘኑ ፣ተስፋ የቆረጡ ግልጽ መሆን አለባቸው ያሏቸውንና ሌሎች ጥያቄዎችንም ያነሱ ይገኙበታል።   
ቤቢሾ ጊዱማን በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት « ተስፋ ጠብቀን ነበር በጣም ያሳዝናል ሲል ይጀምርና «ከዚህ በኋላ መፍትኄ ከእግዚብሔር እንጠብቃለን ስቃያችን በዛ» ካለ በኋላ በእንግሊዘኛ« የሞት ፍርድ ነው። ሰላም አማራጭ ተደርጎ አልተወሰደም፤ መንግሥት የዜጎቹን ሰላም ከማስጠበቅ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ የለውም። ለፖለቲካዊ ጥያቄ ፖለቲካዊ መፍትኄ ፈልጉ ሲል የበኩሉን ማሳሰቢያ አቅርቧል ዳጊ ሰሎሞን «ለጦርነትም፣ ለድርድርም እያላችሁ የሀገር ሀብት ታባክናላችሁ።» ሲሉ ተችተዋል። ማርቆስ ቱሬ ደግሞ መንግሥትን ይወቅሳሉ ።«መንግስት ራሱን መፈተሽ አለበት።ምክንያቱም እንደ መንግስት የህዝቡን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም።ያልሰመረው የመንግስት እና የኦነግ-ኦነሰ ድርድር በህዝብ ደም ለሚጫወት ጠላት የምን ልመና ነዉ? ለጠላት ይሄንን ሚያክል የምን ፕሮቶኮል ነዉ? ውይም እሹሩሩ ነዉ? መንግስት እርምጃ የመውሰድ የአቅም ውስንነት /በራሱ አለመተማመን እና ስጋት አንዳለው የሚያሳይ አካሄድ ነዉ ማለትም ይቻላል።» ሲሉ ገምግመዋል። 

«የንግግሮቹ ይዘት ምንድነው ?? ህዝብ ማወቅ የለበትም ??? በምን በምን ጉዳይ እንዳልተሰማማቹ ማወቅ እንፈልጋለን ፥ ምከንያቱም ሰላም በማጣታችን ሁላችንም እየተጎዳን ነን»
«የተደራዳሪዎች ሚናና የመደራደሪያ ሀሳብ ስላላወቅን እንጂ እኛም እንደ ዜጋ ለሰላም ሲባል የምንለው አይጠፋም ነበር፤ ያም ሆነ ይህ ፣ ከሰው ዕልቂት ይልቅ የትኛውም ጉዳይ ክቡር ከሆነው የሰው ሕይወት ስለማይበልጥ ብንታረቅ ይሻላል ይላል።»ምስል Seyoum Getu/DW

ሸሪፍ አባገላን ቢቸግራቸው ይመስላል "ተመካክረህ አትግባባ፣ ተግባብተህ አትመካከር" ፣ የሚል እርግማን ይኖር ይሆን? ሲሉ የበኩላቸውን መላ ምት አስፍረዋል።የመንግሥትና በአሸባሪነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ድርድሩ መክሸፉንና ንግግሩ ላለመስመሩም ምክንያቶች ያሏቸውን በጥቅሉ ከማሳወቅ ውጭ ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ አላደረጉም። ፋስት ቢላቭድ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ ሀሳብ ይህን ይመለከታል። «የተደራዳሪዎች ሚናና የመደራደሪያ ሀሳብ ስላላወቅን እንጂ እኛም እንደ ዜጋ ለሰላም ሲባል የምንለው አይጠፋም ነበር፤ ያም ሆነ ይህ ፣ ከሰው ዕልቂት ይልቅ የትኛውም ጉዳይ ክቡር ከሆነው የሰው ሕይወት ስለማይበልጥ ብንታረቅ ይሻላል ይላል። መኮንን ሞታሉ ደግሞ ፣ «የንግግሮቹ ይዘት ምንድነው ?? ህዝብ ማወቅ የለበትም ??? ሲሉ ጠይቀዋል። ተገን ባሻም ተመሳሳይ ጥያቄ አላቸው ፣ በምን በምን ጉዳይ እንዳልተሰማማቹ ማወቅ እንፈልጋለን ፥ ምከንያቱም ሰላም በማጣታችን ሁላችንም እየተጎዳን ነን የሚል ። ተደራዳሪዎች ሳይስማሙ ቢለያዩም ተስፋ አያስቆርጥም ፤ አስተያየት ሰጭዎች 

«እርቅ እንደግፋለን ምኑላይ ተስማምታችው ምን ላይ እንዳልተስማማችው ቢገለጽ መልካም ነበር ሲሉ ሃሳባቸውን የጀመሩት በድሩ ሁሴን ይህ ቢደረግ « ለወደፊቱ ጠቃሚ አስተያየቶች ልታገኙ ትችላላችሁ ሲሉ መክረዋል።

መንግሥት ለሚወጋው ኃይል «ኪላሽንኮቭ ታጥቆ ከቴክኖሎጂ ጋር መጋፈጥ ውጤቱ ክፉ ነው» የሚል መልዕክት ተልላፏል
«ተበታትነው በከላሽንኮቭ የሽምቅ ትግል የሚያደርጉ ተዋጊዎችን በድሮን መዋጋት መንግስት የሀገሪቱን ሀብት ምን ያህል እያባከነ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል» ምስል Waghemra Communication office

በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ውጊያ የሚያካሂደው መንግሥት ሸኔ የሚለው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሲልየሚጠራው ቡድን ከሁለት ዓመት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጇል። አሚ አምሀ በፌስቡክ ይህን መነሻ አድርገው «አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ቡድን ጋር መደራደር ይቻላል ?በማለት ጠይቀዋል። 


የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ውጊያ በሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮኖች የሚፈጸሙት ጥቃቶች እንዳሳሰቡት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስታውቋል። ኮሚሽኑ «ጥቅምት 26 በክልሉ በዋደራ ወረዳ በአንድ ትምህርት ቤት ላይ የተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሦስት መምህራንን ጨምሮ 7 ሰዎች መገደላቸውን፣  ጥቅምት 29 በምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋብር ከተማ በመነሃሪያ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 13 ሰዎች መገደላቸውን» ገልጿል። በክልሉም ይሁን በሌሎች አካባቢዎች የቀጠሉ ያላቸው የመብት ጥሰቶችና የዘፈቀደ እሥሮች አሳሳቢነት ከፍ ማለቱንም አስታውቋል።

በአማራ ክልል የሚፈፀም ድሮን ጥቃት እንዳሳሰበው የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለፀ

በዚሁ ጉዳይ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል አንዱ ካሳሁን አስ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ ሀሳብ መንግሥትን በአባካኝነት ይከሳል ።«ተበታትነው በከላሽንኮቭ የሽምቅ ትግል የሚያደርጉ ተዋጊዎችን በድሮን መዋጋት መንግስት የሀገሪቱን ሀብት ምን ያህል እያባከነ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል» ይላል። አለማየሁ ኃይሌ ደግሞ መንግሥት ለሚወጋው ኃይል «ኪላሽንኮቭ ታጥቆ ከቴክኖሎጂ ጋር መጋፈጥ ውጤቱ ክፉ ነው» የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። የተሻለ መፍትኄ ይመጣል ብለው የማያስቡት ጥላዬ ከበደ ደግሞ «ማን ይሰማል ይቀጥላል ዱሮኑ» ሲሉ የበኩላቸውን ግምት በፌስቡክ አካፍለዋል። ነሲቡ ኬ ማራሚ መፍትኄ አቅርበዋል «ድርድር ብቻ» የሚል። ተገኘ ታየው«በኢትዮጵያ በአማራ ክልል ሰላማዊ ሰዎችን በድሮን መግደል አቁሙ» የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ አፍሪካ ምክር ቤት ፕሪቶሪያ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ እንዲዘጋ እና ከእስራኤል ጋር የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሙሉ እንዲቋረጥ መወሰኑ በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ትኩረት ከሳቡት ጉዳዮች አንዱ ነበር።
የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ምስል Esa Alexander/REUTERS

መሀመድ አሊ መሀመድ «ለመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት አለ ወይ?? ሲሉ በምጸት ሲጠይቁ ተካልኝ ተስፋዬም « ድርጅቱ በህይወት አለ? ዓላማው ማሳሰብ ብቻ ነው ? ጥርስ የሌለው የስም አንበሳ " የተባበሩት…ይባላል።በ፪ኛው የዓለም ጦርነት የነበረውን ሚና እየደገመ፣ የአሜሪካ ሞግዚት ሆኖ በጀት ከአሜሪካ እየተሰፈረለት "የተባበሩት"ሲባል ይገርማል? የአማራን፣የጋዛን እና ሌሎችን ጦርነቶች ከማውገዝና አሳስቦኛል ከማለት ውጭ ሚና የሌለው የስም ተቋም ሲሉ ወቅሰዋል ። 

የደቡብ አፍሪካ ምክር ቤት ፕሪቶሪያ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ እንዲዘጋ እና ከእስራኤል ጋር የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሙሉ እንዲቋረጥ መወሰኑ በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ትኩረት ከሳቡት ጉዳዮች አንዱ ነበር ። ውሳኔውን የደገፉም የተቹም አሉ። ቤተ እሥራኤል ኢንዱስትሪ በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ አስተያየት«ከደቡብ አፍሪካ የሚጠበቅ ጥቅምም ጉዳትም የለም ግን ከሃማስ በላይ የእስራኤል ትልቋ ጠላት መሆኗን አስታውቃለች ብሏል። ከድር አህመድ ስማርት ደግሞ « ጎበዝ መሪ ሁሉም ከሱ መማር አለባቸው ለምሳሌ አረብ አገሮች አሜሪካን በመፍራት ምንም መስራት አልቻሉም» ብዙዎች የደቡብ አፍሪቃውን ፕሬዝዳንት ጀግና መሪ ሲሉ አወድሰዋቸዋል። ከመካከላቸው አንዱ ከድር ሁሴን ናቸው።አብዱሳሌም ሹክራላ ውሳኔውን ትክክለኛ ብለዋል።  
«ደቡብ አፍሪካ ለእውነት የቆመች ምን አልባት ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር ብለዋታል ነገን በተስፋ ።

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር