1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

ማላዊ ለምን ወጣቶቿን ለስራ ወደ እስራኤል ትልካለች?

ዓርብ፣ ግንቦት 2 2016

የማላዊ መንግሥት ስምምነቱ ለወጣት ዜጎቹ ጥሩ የሥራ እድል የሚፈጥር ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱም ከውጭ ምንዛሬ ትርፋማ የምትሆንበት ነው ይላል። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን እቅዱን ተችተዋል።

https://p.dw.com/p/4fdJZ
የማላዊ ሰራተኞች በማላዊ
የማላዊ ሰራተኞች በማላዊምስል Michael Runkel/imagebroker/imago images

ማላዊ ለምን ወጣቶቿን ለስራ ወደ እስራኤል ትልካለች?

በማላዊ እና እስራኤል መካከል የተደረገው የአሰሪ እና ሰራተኛ ስምምነት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው ባለፈው ህዳር ወር ነበር። ከዛን ጊዜ አንስቶ ከ700 በላይ ማላዊ ወጣቶች እስራኤል ውስጥ ሥራ ጀምረዋል። ሁለቱ ሀገራት ከሁለት ሳምንታት በፊት ቴላቪቭ  ላይ የተፈራረሙት አዲስ የአሰሪ እና ሰራተኛ ስምምነት ደግሞ ወደ 3,000 የሚጠጉ የማላዊ ችሎታ የሌላቸው ወጣት ሰራተኞች ወደ እስራኤል ተጉዘው በእርሻዎች እና በኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንዲሰሩ ይመለከታል። ማላዊያን በዚህ የሥራ ስምምነት ላይ ያላቸውን አስተያየት የዶይቸ ቬለ 77 ከመቶው የወጣቶች ዝግጅት አጠያይቋል። 

በማላዊ እና እስራኤል መካከል የተደረገው የመጀመሪያ ስምምነት

በማላዊ እና እስራኤል መካከል የተደረገው የመጀመሪያው የአሰሪ እና ሰራተኛ ሥምምነት ለ10 000 ማላውያን የስራ እድል እንደሚፈጥር የማላዊ መንግሥት ለዜጎቹ ሲያስተዋውቅ ቆይቷል።  መርኃ ግብሩ ከጀመረ ገና ሶስት ወር ሳይሞላ የማላዊ የገንዘብ ሚኒስትር ሲምፕሌክስ ቺቲዮላ ባንዳ ህዝቡ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም አትራፊ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህ ፕሮግራም ሀገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዳገኘች እና ከ 735,000 በላይ ዶላር ከሰራተኞች ኤክስፖርት የተገኘ ገንዘብ ወደ ማላዊ መተላለፏንም ይፋ አድርገዋል።  
«በርካታ ወጣት ማላዊያን ተምረው ስራ እንደማያገኙ ሀቅ ነው» የምትለው ማላዊት ክሪሲስ ዚሊናኒ ግን እንደ አንድ ወላጅ፤ ልጇን ወደ እስራኤል መላክ አትፈልግም።
« ልጄንም ሆነ ወይም ሌላ ሰው ልጆቹን ወደ እስራኤል ለስራ እንዲልክ አልመክርም። ስጋቴ ምንድን ነው ፤ ጦርነት ያለበት ቦታ ነው።  ምንም እንኳን ጦርነቱ ያለው ሰዎቹ ከሚሰሩበት ሌላ አቅጣጫ ነው ቢባልም እንደ እናት ልጄን በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ለስራ ልኬ በሰላም ተኝቼ የማድር አይመስለኝም። »

እንደዛም ሆኖ ጉዞውን በጉጉት የሚጠባበቁ ይገኛሉ። በሙያዋ ነጋዴ የሆነችው ግሪስ ባንዳ ምክንያታቸውን ትረዳለች። «ማላዊ ውስጥ ህይወት ከባድ ነው። ሰዎች ወሩ መጨረሻ ለመድረስ ይታገላሉ።  ሰዎች በቀን ሶስቴ ቀርቆ አንዴ የሚበሉት ለማግኘት ትግል ላይ ናቸው። እና እንደዚህ አይነት የሥራ እድል ወደ እስራኤል ሲገኝ ለበርካታ ወጣት ማላዊያን ጥሩ እና የማይገኝ  እድል ይመስላል።»

የሥራ ቅድመ ሁኔታዎቹ እና ውሎች

ግሪስ የስራ እድሉን ወደ እስራኤል ብታገኝ ትጓዝ ይሆን?  አዎ! ትላለች ግሪስ ! ይሁንና መሟላት አለባቸው የምትላቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። « የተጓዥ ወጣቶች  ውሎች እና ቅድመ ሁኔታዎችን በተመለከተ እየተስፋፉ ያሉ ወሬዎች አሉ። ውሎቹ ግልጽ አይደሉም። እዚህ ማላዊ ውስጥ እንግሊዘኛ ሁለተኛ ቋንቋ ነው።  ስለዚህ ለተቀጣሪዎቹ ውሎቹ እና ቅድመ ሁኔታዎቹ በደንብ ሊገለፅላቸው ይገባል።  ምክንያቱም ለምሳሌ እስራኤል ሲደርሱ ደሞዛቸው እዛ አይከፈላቸውም። ገንዘቡ የሚከፈላቸው ሀገራቸው ባለ የባንክ አካውንታቸው ላይ ነው። ታድያ እንዴት ብለው ነው እዛ መቆየት የሚችሉት? »  ለወጣቶች መብት የሚቆረቆረው ጉድፍሪም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳቡ ሁለት ተከፍሏል። 
« በአንድ በኩል ለህዝቡ በጣም ተደስቼ ነበር። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ላይ ስራ አጥነትን መቅረፍ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አውቃለው። » በሌላ በኩል ግሪስ ያነሳችው የውል እና የደሞዝ ጉዳይ ጥርጣሬ ውስጥ ከቶታል። ወጣት ስቲቭን ግን በመርኃ ግብሩ ላይ ያለው አቋም የፀና ነው። እድሉን ቢያገኝ ወደ እስራኤል ይጓዛል። « አዎ እሄዳለሁ።  የምሄደው ነገሮች ከባድ ስለሆኑ ሳይሆን ራሴን በእውቀት ማጎልበት ስለምፈልግ ነው።  ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሀገሬ ተመልሼ እንደምመጣ አውቃለሁ። » 

የእስራኤል ገበሬ
ጦርነት ውስጥ ከተገባ አንስቶ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ ትልቅ ሚና የሚጫወቱት የእስራኤል እርሻ እና ኢንዱስትሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን አጥተዋል።ምስል Menahem Kahana/AFP/Getty Images

ሥራ ጦርነት በሚካሄድባት እስራኤል

እ.ጎ.አ  ጥቅምት 7 ቀን ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረና ጦርነት ውስጥ ከተገባ አንስቶ ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ ትልቅ ሚና የሚጫወቱት የእስራኤል እርሻ እና ኢንዱስትሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን አጥቷል።  ምንም እንኳን ማላዊ 10 ሺህ የሀገሯ ዜጎችን ወደ እስራኤል ለመላክ ትስማማ እንጂ እስራኤል እስከ 100 ሺህ ማላዊያንን የመቅጠር አቅም እንዳላት ማላዊ ጠቁማለች። እስካሁን ድረስ ከዚህ መርኃ ግብር ተጠቃሚ የሆኑት ገጠራማ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ማላዊያን ናቸው ይባላል። 
የተማረውስ የሰው ኃይል በተለምዶ «ዝቅተኛ ስራ» ነው ወደ ሚባልለት የጉልበት ሥራ  ለማግኘት ሲል እየተጓዘ ይሆን? የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ጦርነት ወቅት ዜጎችን ለምን ወደ እስራኤል መላክ አስፈለገም ሲሉ ይተቻሉ። የማላዊ መንግሥት ግን በአንድ ሀገር ላይ ያለው ስጋት ከሚገኘው ጥቅም ጋር ሲነፃፀር ጥቅሙ የሚያመዝን ከሆነ ዜጎቹን ወደ እስራኤልም ሆነ ሌሎች ሀገራት ከመላክ ወደ ኋላ እንደማይል የመንግሥት ቃል አቀባይ ሞሴስ ኩኩንዩ ገልጸዋል። እንደ እሳቸውም የወጣቶቹ ደህንነት በእስራኤል አሁንም የተረጋገጠ ነው። 

«የአፍሪካ መሪዎች ኃላፊነታቸውን አልተወጡም»

ጋናዊው ፕሮፌሰር ፊደል አማካዬ አውሱ ግን የአፍሪካ መሪዎች ለወጣቶች የተሻለ የስራ እድል የመፍጠር ስራቸውን ከመጀመሪያውኑ ተወጥተው ቢሆን ኖሮ ጨርሶንም እንደዚህ አይነት ስምምነት ውስጥ ባልተገባ ነበር ይላሉ።  ወጣቶቹ እስራኤል ሄደው ሰርተው ለሀገራቸውም ሆነ ለራሳቸው ትርፍ ያስገኛሉ ወይም የሥራ እውቀት ይገበያሉ የሚለው ብዙም አያሳምናቸውም። « ዋናው ጥያቄ የማላዊ መንግሥት ወይም ሥርዓት ለወጣቱ የሚያወሩትን አይነት የሥራ እድል አቅርበዋል ወይ?  እንደእዛ ከሆነ ለምን በመጀመሪያ ነገር ወጣቱን ወደ እስራኤል መላክ  አስፈለገ? ሰዎች እውቀቱ አላቸው። ስራ ስላላገኙ ወይም በቂ ክፍያ ስላልተከፈላቸው ብቻ ነው። እኛ አፍሪቃውያኖች አዎ ብዙ ችግሮች አሉብን። ግን የስራ ፈጠራ ላይ ደካማ ነን። ናይጀሪያ ፣ ጋና !   እና ይህን ጥሩ አጋጣሚ የሚል ነገር ትቶ ወጣቶችን እዛው ሀገር ውስጥ ለመጥቀም የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ይሻላል። » 


የማላዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ መንግሥት ጉልበት ያለው ህዝቡን ከሀገር እየላከ በሀገሪቷ ላይ  ሌላ ችግር ይፈጥራል ሲሉ ይተቻሉ።  አስተያየቱን በፁሁፍ ለዶይቸ ቬለ ያጋራው  ባቢላ ኑምቪ ግን በማላዊ ያለውን የሥራ አጥነት ጫና ይቀንሳል በማለት መርኃ ግብሩን ይደግፋል፤  ተቃዋሚዎችን ይተቻል። «የዚህ ሁሉ ተቃዋሚ ፓርቲ ችግር ምን እንደሆነ አይገባኝም። መንግሥት እያደረገ ያለውን ማንኛውንም ነገር ፈጽሞ አያደንቁም።»  ባይ ነው። 

ሥራ አጥነት በሊቢያ
ሥራ አጥነት በሊቢያ፤ ሥራ አጥነት በማላዊ ብቻ ሳይሆን የበርካታ አፍሪቃ ሀገራት ዋንኛ ችግር ነው።ምስል picture alliance/chromorange/G. Fischer

«ከማላዊ ወጣት የስራ እድል የሚያገኘው 3 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው » የሚለው የወጣቶች መብት ተቆርቋሪ ጎድፍሪ ይህን የስራ እድል ተመራጭ የሚያደርገው ነገሮች ቢኖሩም የሀገሩ መንግሥት ጉዳዩን ያስተናገደበት መንገድ አላስደሰተውም። «መንግሥት ጉዳዩን ያስተናገደበት መንገድ አላስደሰተኝም። መረጃው ለህዝብ ይፋ መሆን ነበረበት።  አሉባልታ ወሬ እንዲፈጠር ክፍተት መፍጠር አልነበረበትም። » በርካታ ማላዊያን መርኃ ግብሩን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸውም መንግሥት ጉዳዮን ይፋ ከማድረጉ በፊት በሀገሪቱ ያሉ አንድ የተቃዋሚ ፖርቲ መሪ ጉዳዩን ጥያቄ ውስጥ ከከተቱ በኋላ መሆኑ ነው። የተቃዋሚ መሪ ኮንድዋኒ ናንክሁምዋ  በጋዛ ጦርነት ወቅት መንግስት ሰራተኞችን ወደ እስራኤል ሊልክ ማቀዱ 'ክፉ ግብይት' ነው ሲሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርላማ ላይ ተችተዋል።

ሕጋዊ የሆነ የእርሻ ቦታ ሥራቸውን ትተው ዳቦ ቤት የጀመሩ ማላዊያን

ይህ እንዲህ እንዳለ ማላዊ ከእስራኤል ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቷን አጥብቃለች። ከሁለት ሳምንት በፊት ቴላቪብ ላይ የማላዊ ኤምባሲ ሲከፈት ሁለቱ ሀገራት አዲሱን እና 3,000 የሚጠጉ የማላዊ ወጣት ሰራተኞችን የሚመለከተውን ውል ተፈራርመዋል።  ብዙም ሳይቆይ በዚህ ሳምንት እስራኤል 12 የማላዊ እርሻ ሰራተኞችን ወደ ሀገራቸው መልሳለች። ማክሰኞ ዕለት የማላዊ የመንግሥት ቃል አቀባይ ሞሴስ ኩኩንዩ በሰጡት መግለጫ ውላቸውን በመጣስ፣  ሕጋዊ የሆነ የእርሻ ቦታ ሥራቸውን ትተው ዳቦ ቤት መሥራት የጀመሩ 12 ማላዊያን ወደ ሀገራቸው ተመላሽ ሆነዋል። ኩኩንዩ ሌሎች እስራኤል የሚገኙ ማላዊያን የሀገራቸውን ስም ከሚያስጠፉ ድርጊት እንዲቆጠቡ በማሳሰብ የኮንትራቱን ውል የሚጥስ ሰራተኛን መንግሥታቱ "እንደማይታገሱም" አስጠንቅቀዋል።
እንደ ግሪስ በእርሻ እና በኢንዱስትሪ ስም ሀገሪቱን ለቆ የሚሄደው ውድ የሀገሪቱ የተማረ የሰው ኃይል ነው። ስለሆነም ሊታሰብበት ይገባል። « ኤክስፖርት የምናደርጋቸው ከሆነ፣ ሀገር ለቀው እንዲሄዱ የምናደርጋቸው ከሆነ ይህችን ሀገር ማን ያለማታል? አብዛኞቹ እነዚህ የሚሄዱ ሰዎች የተማሩ ሰዎች ናቸው። በተለያዩ የስራ ዘርፎች ልምድ ያካበቱ ናቸው። እንደዚህ አይነት ሰዎች እዚህ ማላዊም ያስፈልጋል። »
አፍሪቃ ላይ የሚበረታው ሥራ አጥነት

ለዶይቸ ቬለ 77 ከመቶው ዝግጅት በፌስ ቡክ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አሞስ ቦቢ እባካችሁ ወደ ላይቤሪያ መጥታችሁ ሌሎች 10 ሺህ ወጣቶችን መልምሉ ሲል፤ ሄዝቦን ደግሞ እስራኤል በአሁኑ ሰዓት ለዜጎቿም በአሁኑ ሰዓት አስተማማኝ እንዳልሆነ ስጋቱን ይገልፃል። ከ 200 ሺህ በላይ እስራኤላውያን በጦርነት ከቀያቸው ተፈናቅለው ባሉበት ሁኔታ ለማዊያን ወጣቶች ምን ያህል አስተማማኝ ቢሆን ነው?  ሲልም ይጠይቃል።

ልደት አበበ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር