1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaረቡዕ፣ ሚያዝያ 9 2016

https://p.dw.com/p/4etXf

የአማራ ክልል መንግስት «ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል» ሲል ከሰሰ። የክልሉ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ  «ከትናንቱ ታሪካዊ ስህተቱ መማር ተስኖታል» ያለውን «ህወሓት ህዝባችን ላይ ወረራ ፈጽሟል » ብሏል።

ህወሓት ወረራ የፈፀመባቸው ያላቸው የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረምና ዛታ እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት አካባቢዎች መሆናቸውን የጠቀሰው መግለጫው የፌዴራል መንግስት እና ዓለማቀፉ ህብረተሰብ ድርጊቱን እንዲያወግዙ እና እንዲያስቆሙ ጠይቋል።

በደቡብ ትግራይና በሌሎች በኃይል በተያዙ የትግራይ ግዛቶች፥ እየታየ ያለው ክስተት በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር አልያም በህወሓት፥ ወይም ደግሞ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት እንዳልሆነ የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት ማክሰኞ በትዊተር ባጋሩት መረጃ አስታውቀው ነበር።

ነገር ግን ሰሞኑን የህወሃት ኃይሎች በራያ አላማጣ አካባቢ አንዳንድ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ የአጎራባች ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች መሰደዳቸውን ከየአካባቢው ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ ።

 

ከራያ አላማጣ ሰሞኑን የተፈናቀሉ ወገኖች ያለ ምግብና በቂ መጠለያ ቆቦ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ሞቃታማ  ቦታ እንዲሰፍሩ መደረጋቸውን ተናገሩ። የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከል ጽ/ቤት በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎች  ከ30 ሺ በላይ ማሻቀቡን አስታውቋል።  ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት የአካባቢው አስተዳደር  ተገቢውን ድጋፍ አላቀረበላቸውም።  ህዝብና መንግስት አስፋላጊውን ሰብአዊ በአፋጣኝ እንዲያቀርቡላቸውም ጠይቀዋል፡፡
«የሆነ መጠለያ ነገር ከከተማው ወጣ ያለ ነገር የሆነ ኢንዱስትሪ ፓርክ ነው ምናምን የተባለ ነገር ምንም ሰው የሌለበት እዚያ ሁኑ አሉ፤ ግን የሚገርምህ ለአደጋ የተጋለጠ ቢያንስ በከተማው ዙሪያ ባሉ  ትምህርት ቤቶች እንኳ መሆን እየተቻለ በበረሃ ነው ያለው ነገሩ ። ምንም አቅርቦት የለ፤ እስካሁን እንዴት ሆናችሁ ያለም አካል የለም። »
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር  ትናንት 14 ሺህ 500 ተፈናቃዮች ቆቦ ከተማ መግባታቸውን ጠቁመው ቁጥሩ ዛሬ እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ድረስ የተፈናቃዮች ቁጥር ከ30 እስከ 40 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ለባህርዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ነግረዋል፡፡ 
« አሁን ባለው ሁኔታ ወደ 21,116 አካባቢ የሚደርሱ ህዝብ ነው እየገባ ያለው በቦታው በየቀበሌው ተበትሎ ያለም አለ ገና እስu ሲጨመር ከ30 ሺ እና ከ40 ሺ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ከተማ ይገባሉ የሚል እሳቤ ነው ያለው ፤ የወልድያ ከተማም አሁን ቀድመው የመጡ ተፈናቃዮች አሉ። ወልድያ ያሉትን ወደ አንድ የመሰብሰብ ስራ እየሰራን ነው»
ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በራያ ቆቦ ወረዳ በተቀሰቀሰ አዲስ ግጭት አብዛኛው የወረዳው አካባቢዎች በትግራይ ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ የክልሉ መንግስት በመግለጫው የማንነት ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ውዝግብ የሚፈታው በፕሪቶሪያው ስምምነት በመሆኑ የትግራይ ኃይሎች ሰሞኑን በኃይል ከያዟቸው አካባቢዎች እንዲወጡ ጠይቋል፡፡
 

ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ የተገደሉ የፋኖ አባላት አስክሬን አግኝተው መቅበር እንዳልቻሉ ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ። ካለፈው ቅዳሜ አንስተው የፌዴራሉንም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ እየተመላለሱ መጠየቃቸውን የሚገልጹት የሟቾች ቤተሰቦች የልጆቻቸውን አስክሬን ወስደው ለመቅበር ያደረጉት ጥረት አልሰመረም ይላሉ ። 
አዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ ከተገደሉት አንዱ የነበረው የናሁሰናይ አንዳርጌ ቤተዘመድ የሆኑ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ግለሰብ  እናትየው የልጃቸውን አስክሬን ለመረከብ ወደ ፖሊስ ቢመላለሱም እንዳልተሳካላቸው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። 
«አሁን ዛሬ ያለው አዲስ ነገር ሳይሆን እስካሁን በነበረው አካሄድ ነው እየሄደች ያለው ። ከቅዳሜ ጀምሮ መጀመሪያ የጀመረችው አዲሳ አበባ ፖሊስ ነው። እሱ እኛን አይመለከትም ብሎ ትናንትም ስትሄድ ጭራሽ አላስገባ ብለው በበር ላይ በመከራ አልቅሰው ነው የገቡት። በመጨረሻም ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ተባሉ ፤ ከዚያም ሲሄዱ ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ የሚሰጥ አካል አላገኙም ።» 
የልጆቻቸውን አስክሬን አግኝተው መቅበር ያልቻሉ ወላጆች ጭንወት ውስጥ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የአዲስ አበባው ወኪላችን ስዩም ጌቱ  በጉዳዩ ላይ ከፌዴራልም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ቃል የህዝብ ግንኙነት ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት ስልክ ለመደወል ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ «ናሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ የተባለው የፅንፈኛው ቡድን አመራር እና አቤነዘር ጋሻው አባተ የተባለ የቡድኑ አባል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ሕጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው» መሆኑን ገልጾ  « ሀብታሙ አንዳርጌ ተሰማ የተባለው የቡድኑ አባል ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ነው» ብሏል። 
 

ኢራን  ከእስራኤል ሊሰነዘር የሚችል ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ነኝ አለች። የኢራን የየር እና የባህር ኃይላት ከእስራኤል የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን በየፊናቸው ገልጸዋል። የኢራን የጦር ኃይላቱ ዝግጁነታቸውን ያስታወቁት እስራኤል የጦር ካቢኔ ዛሬ በኢራን ላይ ሊወሰድ በሚገባ የአጸፋ ጥቃት አይነት ላይ መወያየቱን ተከትሎ ነው።

የኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራኢሲ በሀገሪቱ ወታደራዊ ቀን ላይ ዛሬ ባደረጉት ንግግር  « ከጽዮናዊቷ ሀገር  የሚቃጣብን የትኛውም ጥቃት አጸፋው የከፋ ይሆናል » በማለት አስጠንቅቀዋል። የሀገሪቱ የአየር እና የባህር ኃይላትም በየፊናቸው ጥቃቶቹን ለመመከት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

የሀገሪቱ አየር ኃይል ሩስያ ሰራሽ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችን ጨምሮ በታጠቃቸው መሳሪያዎች እስራኤልን ለመጋፈጥ መዘጋጀቱን አስታውቋል። የሀገሪቱ ባህር ኃይል በበኩሉ የኢራን የንግድ መርከቦችን በቀይ ባህር ላይ ማጀብን ጨምሮ የሚሰነዘሩ ጥቃቶን ለመመከት መዘጋጀቱን ያስታወቀው። ኢራን ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት ከ300 በላይ ድርኖች እና ሚሳኤሎች  በጥምረት በእስራኤል ላይ አስወንጭፋለች ።

ምንም እንኳ እስራኤል ከተቃጣባት የአየር ጥቃት 99 በመቶውን ማክሸፏን ብትገልጽም ። ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል ከዋነኛዋ አጋሯ አሜሪካ ድጋፍ ባታገኝም በኢራን ላይ የአጸፋ ጥቃት ለመሰንዘር አማራጮችን እያጤነች ነው።

 

 

የኢትዮጵያ የሚንስትሮች ምክር ቤት በሀገሪቱ የሽግግር ፍትህ የሚመራበትን ረቂቅ ፖሊሲ አጸደቀ። ምክር ቤቱ ፖሊሲውን ያጸደቀው 30ኛውን መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ባካሄደበት ወቅት ነው።

ፖሊሲው በሀገሪቱ በዘመናት ሂደት የተከሰቱ ብሎም እየቀጠሉ ያሉ ለሰብአዊ መብቶች መጣስ እና የእርስ በእርስ ግጭቶች ምክንያት የሆኑ ትርክቶችን ለመፍታት እንደሚያስችል የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ አጋርቷል።

 ቀደም ሲል የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችንም ሆነ የእርስ በእርስ ግጭቶች ለመፍታት በግልፅ ፖሊሲ የሚመራ ሁለንተናዊ የሽግግር ፍትሕ ስልትን አካታች፣ ሰብአዊ መብት ተኮር በሆነ እና በተሰናሰለ መንገድ ባለመተግበራቸው የሚፈለገውን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አለመቻላቸውን መግለጫው አመልክቷል።

በዚህም  የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን በተደራጀ፣ በተቀናጀ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመምራትና ለመተግበር እንዲቻል ምክር ቤቱ ረቂቅ ፖሊሲውን መርምሮ ማጽደቁን አስትቋል።

 ፖሊሲውም ከጸደቀበት ዕለት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን መግለጫው አመልክቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚንስትሮች ምክር ቤት  በ2010 ዓ.ም ጸድቆ ስራ ላይ የዋለው የመንግስት ሠራተኞች አስተዳደር አዋጅ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽነት እና ተጠያቂነት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ያለውን ረቂቅ ፖሊሲ መርምሮ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱን አስታውቋል።

 

 

በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ፣ ባህሬን እና ኦማን ብርቱ አውሎነፋስ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ለ20 ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆነ።  በኦማን የተከሰተው አውሎ ነፋስ እና የጎርፍ መጥለቅ ህጻናትን ጨምሮ 19 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።  በዓለማቀፍ የቱሪስት መዳረሻዋ እና የፋይናንስ ማዕከሏ የዱባይ ከተማ  ደግሞ እስካሁን በተሽከርካሪያቸው ውስጥ እያሉ በጎርፉ የተወሰዱ  አንድ የ70 ዓመት አዛውንት ህይወታቸው ማለፉ መረጋገጡን  የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በከተማዋ 254 ሚሊ ሜትር መጠን የተመዘገበበት ዝናብ ያስከተለው ጎርፉ ተሽከርካሪዎችን ከአውራጎዳናዎች ላይ እያንከባለለ ሲወስድ ታይቷል። በተጨማሪም  የአየር እና የየብስ መጓጓዣ ማስተጓጎሉ ተገልጿል። በዚህም በርካታ ዓለማቀፍ በረራዎች መሰረዛቸውን ተከትሎ ለወትሮ በመንገደኞች የሚጨናነቀው የዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ ተጓዦችን ባላችሁበት ቆዩ ብሏል።

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እንደሀገር ከተመሰረተች ከ1949 ወዲህ ከፍተኛ ዝናብ እና የጎርፍ መጥለቅለቅ ሲመዘገብ ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሎለታል ።

 ወጀብ የቀላቀለው ኃይለኛ ዝናብ የዓለማቀፉ የዓየርን ንብረት ለውጥ ያመጣው መዘዝ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

ሩስያ በታሪካዊቷ የዩክሬን ከተማ ቼርኒጊቭ ከተማ ሶስት ክሩዝ ሚሳኤሎች አስወነጨፈች ። በጥቃቱ በትንሹ 16 ሰዎች ተገድለዋል፤ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል። ጥቃቱን ተከትሎ ጎዳናው የተጎዱ ሰዎችን ወደ ህክምና ለማድረስ በሚሯሯጡ ሰዎች እና ከፍርስራሾች ስር በህይወት የተረፉ ሰዎችን በሚያፈላልጉ ሰዎች ተሞልተው እንደነበር ተንቀሳቃሽ ምስሎች አሳይተዋል። የሩስያ የዛሬው ጥቃት ዩክሬን ከአጋሮቿ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ እየጠየቀች ባለችበት ወቅት የተፈጸመ ነው ተብሏል። በከተማዋ ሰሜናዊ ማዕከላዊ ክፍል የነበሩ ህንጻዎች ተደርምሰዋል ፤ በጎዳናዎች ዳርቻ የነበሩ ተሽከርካሪዎችም ወድመዋል። በፍርስራሾች ስር የተቀበሩ ሰዎችን የማፈላለጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያመለከቱት ባለስልጣናት ምናልባትም የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ስጋትም አሳድሮባቸዋል።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
Mittelmeer | Asylreform in der EU
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።