1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዚያ 29፣2016 የዓለም ዜና

Negash Mohammedማክሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2016

-መንገደኞችን አሳፍሮ ከሐዋሳ ወደ አዲስ አበባ ይበር የነበረ አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ላይ እያለ የተፈጠረበት ጢስና መንጋጫገጭ መንገደኞችን ማስጋትና ማስጨነቁ ተነገረ።አዉሮፕላኑ አደጋ ሳይደርስበት አዲስ አበባ አርፏል።-የእስራኤል እግረኛ ጦር በሕዝብ የተጨናነቀችዉን የጋዛ የጠረፍ ከተማ ራፋሕን ለመዉረር መዘጋጀቱ አለም አቀፍ ሥጋትና ዉጥረት አስከትሏል።የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአዉሮጳ ሕብረት ራፋሕ እንዳትወረር አሜሪካ ጣልቃ ትገባ ዘንድ እየተማፀኑ ነዉ።-የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግስታቸዉ ከምዕራባዉያን ባለንጦቹ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/4fbLy

ሐዋሳ- የመገደኞች አዉሮፕላን ጤሰ፣ የደረሰ ጉዳት ግን የለም

 

መንገደኖችን አሳፍሮ ከሐዋሳ ወደ አዲስ አበባ ይበር የነበረ አንድ አዉሮፕላን በረራ ላይ እያለ የተፈጠረበት ጢስ መንገዶችን ማስደንገጡን ተሳፋሪዎች አስታወቁ።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነዉ የበረራ ቁጥር ኢቲ 154 አዉሮፕላን መጤስ የጀመረዉ በረራ ከጀመረ ከ10 ደቂቃ ግድም በኋላ ነዉ።የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ እንዳስታወቀዉ ጢሱ በመንገደኞቹም ሆነ በአዉሮፕላኑ ላይ ምንም ጉዳት ሳያደርስ አዉሮፕላኑ አዲስ አበባ አርፏል።አቶ ብሩክ ቡልቻ የተባሉ መንገደኛ እንዳሉት ግን መንገደኛዉ አዲስ አበባ የደረሰዉ ሕፃናት እያለቀሱ፣ አዋቂዎች  ከጭንቀትና ፀሎት ሳይለዩ ነዉ።

 

አቶ ብሩክ አክለዉ እንዳሉት አዉሮፕላኑ በረራ ላይም እያለ ሆነ ካረፈ በኋላ ጢስ ያወጣበትን ምክንያትም ያስረዳቸዉም፣ በጭንቀት የተዋጡትን መንገደኞች ያፅናናም ወገን የለም።የሐሳዉ ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ እንደዘገበዉ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተፈጠረዉ ችግር መንገደኞቹን ይቅርታ ጠይቋል።አዉሮፕላኑ አሳፍሯቸዉ የነበሩ ሰዎችን ብዛትና የበረረበትን ሰዓት የሐዋሳዉ ወኪላችን ዘገባ አልጠቀሰም።

 

ናይሮቢ-የሶማሊያ መንግስት ጦር ሰላማዊ ሰዎችን ገደለ-አምንስቲ ኢንተርና ሽናል

የሶማሊያ መንግስት ጦር  ባለፈዉ መጋቢት የታችኛዉ ሸበሌ በተባለዉ ግዛት በሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) ባደረሰዉ ድብደባ 23 ሰላማዊ ሰዎች መግደሉን አምንስቲ ኢንተርናሽናል አጋለጠ።ዓለም አአፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ነዋሪዎችን ጠቅሶ ዛሬ እንደዘገበዉ ጦሩ ሰላማዊ ሰዎችን የገደለዉ በታችኛዉ ሸበሌ ግዛት፣ ባግዳድ በተባለዉ መንደር ላይ ሁለቴ በከፈተዉ ጥቃት ነዉ።የሶማሊያ መንግስት ጦር በቅርቡ በታጠቃቸዉ ቱርክ ሰራሽ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች የአሸባብ አባላት ወይም ደጋፊዎች በሚላቸዉ ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እየከፈተ ነዉ።ጦሩ 23ቱን ሠላማዊ ሰዎች የገደለዉ፣ ባካባቢዉ የመንግስት እግረኛ ጦርና የአሸባብ ታጣቂዎች ጠንካራ ዉጊያ ካደረጉ በኋላ ነዉ።የአምንስቲ ኢንተርናሽናል መርማሪዎች 12 ሰዎችን አነጋግረዉ ሰበሰብነዉ ባሉት መረጃ መሠረት ከተገደሉት ሰዎች  14ቱ ሕፃናትና ልጆች ናቸዉ።ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ግድያዉ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል።

 

ዤኔቭ/ የተለያዩ-የጋዛ መዘጋት፣ የራፋሕ ወረራ ሥጋት

 

የእስራኤል እግረኛ ጦር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጤማዉያን ተፈናቃዮች ተጨናንቀዉ የሠፈሩባትን የጋዛ ደቡባዊ ከተማ ራፋሕን ለመዉረር መዘጋጀቱ ዓለም አቀፍ ሥጋትና ተቃዉሞ አስከትሏል።የእስራኤል ጦር የራፋሕ ነዋሪዎችና እዚያ የሰፈሩ ተፈናቃዮች ከተማይቱን ጥለዉ እንዲወጡ ከትናንት ጀምሮ እያሳሰበ ነዉ።ዛሬ ደግሞ ለችግረኛዉ ሕዝብ ርዳታ የሚገባበትን የራፋሕ ማቋረጫን ሙሉ በሙሉ መዝጋቱን አስታዉቋል።የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) ቃል አቀባይ የንስ ሌርክ እንዳስታወቁት «የጋዛ የደም ቧምቧ» ያሉት መስመር  ሙሉ ሙሉ ተቆርጧል።

«ባሁኑ ወቅት ራፋሕ መተላለፊያ መድረስ አንችልም።ምክንያቱም ርዳታ ለማስተባበር ወዲያዚ አካባቢ እንዳንደርስ የእስራኤል መንግስት ሥለከለከለን ነዉ።ይሕ ማለት ባሁኑ ወቅት ወደ ጋዛ ርዳታ ለማድረስ የሚያገለግሉት ሁለቱ የደም ሥሮች ተቆርጠዋል።»

የእስራኤል እግረኛ ጦር በሌሎች የጋዛ ከተማና አካባቢዎች እንዳደረገዉ ግብፅን የምታዋስነዉን ራፋሕን ከወረረ እስካሁን ከደረሰዉ የከፋ ሰብአዊ እልቂት ያስከትላል የሚል ሥጋት አሳድሯል።የፍልስጤም ራስ-ገዝ መስተዳድር የእስራኤል ጦር ራፋሕን እንዳይወር ዩናይትድ ስቴትስ ባስቸኳይ ጣልቃ እንድትገባ ተማፅኗል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በበኩላቸዉ በእስራኤል ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ ወገኖች ተጨማሪ እልቂትን ለመከላከል የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፍ ቦርየል ደግሞ እስራኤል ራፋሕን እንዳትወር ሕብረታቸዉና ዩናይትድ ስቴትስ መጠየቃቸዉን አስታዉቀዋል።

 

ዱባይ-አንዲት መርከብ አጠገብ ከፍተኛ ፍንዳታ ደረሰ

የአደን ባሕሬ ሠላጤን ለማቋረጥ በመቅዘፍ ላይ በነበረች አንዲት የንግድ መርከብ አጠገብ ዛሬ ሁለት ከፍተኛ ፍንዳታ መድረሱን የብሪታንያ የባሕር ላይ ደሕንነት ድርጅት አስታወቀ።UKMTO በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የብሪታንያ የባሕር ንግድ ደሕንነት መቆጣጠሪያ እንደሚለዉ ፍንዳታዉ ከመርከቢቱ በቅርብ ርቀት ላይ ቢደርስም በመርከቢቱና ሠራተኞቿ ላይ ያደረሰዉ ጉዳት የለም።የየመን ሁቲዎች እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ የምትፈፅመዉን ግፍ ለመበቀል የአደን ባሕረ-ሠላጤና ቀይ ባሕርን አቋርጠዉ ከና ወደ እስራኤል የሚቀዝፉ መርከቦችን በተደጋጋሚ ያጠቃሉ። ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያና ተባባሪዎቻቸዉ «የሁቲዎቹን ጥቃት ለመከላከል» ባሉት ዘመቻ ካለፈዉ ታሕሳስ ጀምሮ የሁቲዎች ይዞታ ያሉትን የየመንን ግዛት በተደጋጋሚ ደብድበዋል።ሁቲዎች በመርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃትና እገታ ወደ ሜድትራኒያን ባሕርም እንደሚያስፋፉ ባለፈዉ አርብ አስጠንቅቀዋል።የብሪታንያዉ የባሕር ደህንነት ተቆጣጣሪ ድርጅት ዛሬ የደረሰዉን ፍንዳታ የተኮሰዉን ወገንም ሆነ የመርከቧን ባለቤትና ስም አልጠቀሰም።

 

ዱባይ-ሁቲዎች «የአሜሪካና የእስራኤል ሠላዮች ያዝን» አሉ

በሌላ ዜና አብዛኛ የመንን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ለዩናይትድ ስቴትስና ለእስራኤል መረጃ ያቀብል ነበር ያሉትን የሰላዮች መረብ መበጣጠሳቸዉን አስታወቁ።በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት ሁቲዎች የጋዛዉ ጦርነት ከተጀመረ ወዲሕ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከእስራኤልና ከተባባሪዎቻቸዉ ጋር የገጠሙት ጠብ ክፉኛ ተካርሯል።የሁቲዎችን ወታደራዊ እንቅስቃሴና መረጃን እያጮለጉ ለአሜሪካና ለእስራኤል ሲያቀብሉ የተያዙ «ሰላዮች»  የተባሉ ሰዎችን ምሥል የየመኑ ዜና አገልግሎት ሳባ አሰራጭቷል።የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበዉ ሳባ የተያዙትን ሰዎች ብዛት  አልጠቀሰም።ይሁንና ሳባ ያሰራጨዉ ቪዲዮ የ18 ሰዎችን ምሥል እንደሚያሳይ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

 

ሞስኮ-ፕሬዝደንት ፑቲን አዲሱን ዘመነ-ሥልጣናቸዉን ጀመሩ

ሩሲያ ዉስጥ ባለፈዉ መጋቢት በተደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ያሸነፉት የሐገሪቱ የእስካሁን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ አዲሱን አምስተኛ ዘመነ ሥልጣናቸዉን በይፋ ጀመሩ።በመጋቢቱ ምርጫ ፑቲን ካጠቃላዩ ድምፅ 88 ከመቶ ማግኘታቸዉን የሐገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን አስታዉቋል።ሩሲያን ለረጅም ጊዜ የመሩት ፑቲን  ጠንካራ ተፎካካሪ አልገጠማቸዉም ይባላል።የ71 ዓመቱ አዛዉንት ከእንግዲሕ ለ6 ዓመታት የሚቆየዉን አዲሱን ዘመነ ሥልጣናቸዉ ሲጀምሩ እንዳሉት መንግስታቸዉ ከምዕራባዉያን መንግስታት ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነዉ።

«ሩሲያን እንደ አስተማማኝና ቅን ወዳጅ ከሚያዩት ሐገራት ጋር ያለንን ጥሩ ግንኙነት ለማጠናከር እስካሁንም ወደፊትም ዝግጁ ነን።እነዚሕ ሐገራት ከዓለም አብዛኞቹ ናቸዉ።ከምዕራባዉያን ጋር መደራደርን ዉቅድቅ አናደርግም።ምርጫዉ የነሱ ነዉ።የሩሲያን ዕድገት ለማሰናከል መሞከራቸዉን ይቀጥላሉ? የወራሪነት መርሐቸዉን፣ በሐገራችን ላይ ለዓመታት ያደረጉትን ግፊት ይቀጥላሉ? ወይስ የትብብርና የሰላምን መንገድ ይመርጣሉ?እንደግመዋለሁ፣ የፀጥታና የሥልታዊ መረጋጋትን ጨምሮ መወያየት ይቻላል።ግን በኃይል ሚዛን ላይ ተመሥርቶ መሆን የለበትም።»

የሩሲያ ጦር ዩክሬንን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ ሩሲያና ምዕራባዉያን መንግስታት በጠብ እየተፈላለጉ ነዉ።ዩክሬንን የሚደግፉት ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ሩሲያ ዉስጥ ባለፈዉ መጋቢት የተደረገዉን ምርጫ ዉጤት አልተቀበሉትም።ዛሬ በተከበረዉ በፕሬዝደንት ፑቲን በዓለ ሲመትም ላይ ተወካዮቻቸዉን አልላኩም።

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።