1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ግጭትና ላሊበላ

ዓርብ፣ ጥቅምት 30 2016

በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ለወራት እየተደረገ ያለው ግጭትና ውጊያ አሁንም ስለመቀጠሉ ፣ከፍተኛ ሰብዓዊ ውድመት እያደረሰ ስለመሆኑና መደበኛ የሕይወት እንቅስቃሴ እየታጎለ ስለመሆኑ የየአካባቢው ነዋሪዎች እየገለፁ ነው።

https://p.dw.com/p/4YftK
የፋኖ ታጣቂ
ከፋኖ ታጣቂዎች አንዱ-ላሊበላምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

በአማራ ክልል የሚደረገዉ ግጭትና ላሊበላ

 

በታሪካዊቱ የላሊበላ ከተማና አካባቢዋ በተደጋጋሚ የሚደረገዉ ዉጊያ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡትን ዉቅር አብያተ ክርስቲያን ለአደጋ ማጋለጡን ነዋሪዎች አስታወቁ።ከዚሕ ቀደም በኢትዮጵያ መንግስት፣ በተባባሪዎቹና በህወሓት ኃይላት መካከል፣ አሁን ደግሞ በመንግስትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚደረግ ዉጊያ የከተማይቱ ነዋሪዎችና ቅርሶች ለአደጋ ተጋልጠዋል።ነዋሪዎቹ እንደሙሚሉት ባለፈዉ ሮብ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች ላሊበላን ለመያዝና ላለማስያዝ በገጠሙት ዉጊያም ሁለቱም ወገኖች ለሰላማዊ ሰዎችና ለቅርሶቹ ያደረጉት ጥንቃቄ አልነበረም።በአማራ ክልል በሌሎች አካባቢዎችም ግጭቱ እንቀጠለ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ረቡዕ ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ላሊበላ ከተማ ውስጥ በተደረገ ዉጊያ በቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ግቢ ውስጥ "ሦስት እርሳሶች እንደወደቁ በዐይኔ አይቻለሁ" ሲሉ ጦርነቱ በጥንታዊው ቅርስ ላይ አደጋ መደቀኑን አንድ የዐይን እማኝ ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። 

በሁለቱም ወገን ለቅርሱ ያሰበ አካል የለም የሚሉት እኒሁ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ ሰው፤ ቅርሱ ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖር አለመኖሩ የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም "በሁለቱም ወገን ተከስ ሲካሄድ ፣ ከባድ መሣሪያዎች ይተኮሳሉ ፣ ንዝረትም አለው" ብለዋል። 

ተደጋጋሚዉ ግጭቱን ሕዝብና ቅርሶችን አስግቷል
ተደጋጋሚ ግጭት የተደረገባት የላሊበላ ከተማምስል Annabelle Steffes-Halmer/DW

በአማራ ክልልበመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል ለወራት እየተደረገ ያለው  ግጭትና ውጊያ አሁንም ስለመቀጠሉ ፣ከፍተኛ ሰብዓዊ ውድመት እያደረሰ ስለመሆኑና መደበኛ የሕይወት እንቅስቃሴ እየታጎለ ስለመሆኑ የየአካባቢው ነዋሪዎች እየገለፁ ነው።

ሕወሓት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ጦርነት ውስጥ በነበረበት ወቅት እየተፈራረቁ ሲቆጣጠሯት የነበረችውና በጎብኝዎች ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ያላት ጥንታዊት ላሊበላ ከተማ አሁን ደግሞ ፋኖ እና መከላከያ እየተፈራረቁ እየያዟት ስለመሆኑና በዚህ ሁሉ መፈራረቅ የአካባቢው ሕዝብ ለከፋ ቀውስ እና ችግር እየተጋለጠ መሆኑን ነዋሪዎች እየገለፁ ነው። 
"ለቅርሱ ደህንነት ማንም ያሰበ የለም በሁለቱም አካል። በሁለቱም ወገን ተኩስ ሲካሄድ ከባድ መሣሪያዎች ይተኮሳሉ። ንዝረት አለው። ረቡዕ በነበረው ጦርነት ላይ ከባድ ነገር እንደነበር ነው የሚያሳየው። ገና ግን ምን ይጎዳ ፣ ምን ይጎዳ የተረጋገጠ ነገር የለም። ብቻ እርሳሶች ፣ ሦስት እትሳሶች እንደወደቁ በዐይኔ አይቻለሁ"

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ  ባደረገው ግምገማ "ሊፈርስ ተቃርቦ የነበረውን ክልል ከመፍረስ መታደግ መቻሉ ተረጋግጧል ፤ አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሰዋል" በማለት ክልሉን የሚገኝበት ያሉትን ነባራዊ ሁኔታ ገልፀው ነበር።
ያነጋገርናቸው የላሊበላ ከተማ ነዋሪ እንደሚሉት ትናንት በከተማው የነበሩ "የፋኖ  ታጣቂዎች ወጥተው ሄደዋል"

ከቀናት በፊት በጎጅም - ቡሬ ፣ በሰሜን ሸዋ  - ሸዋ ሮቢት ፣ በወሎ - ላሊበላ ፣ በጎንደር - ወረታ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በከተሞች አካባቢ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሚገኙ ፣ የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ ከከትሞች ወጣ ባሉ ገጠራማ ስፍራዎች እንደሚንገኙ ገልፀው ግጭቶችና ውጊያዎች አሁንም መኖራቸውን ተናግረዋል። ዛሬ ያነጋገርናቸው በጎጃም የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ ሰሞነኛው ውጊያ ሕዝብን ወደ ጫካ ያሸሸ ሆኗል።
ግጭቱ መበርታቱ ከሚነገርበት ከጎጃም አካባቢ አንዱ የቡሬ ከተማ ነዋሪ "የሚተኮሰው ከባድ የጦር መሣሪያ ቤት ላይ ማረፍ ጀምሯል። ሕፃናትና አረጋዊያን ሳይቀሩ ነው እየተመቱ ያሉት። ብለውን ነበር። 
ጦርነቱ በታጣቂ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን በሰላማዊውና ባልታጠቀው ሕዝብም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው ሲሉ ሰሞኑን የተናገሩት ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው "ጥንቃቄ በጎደለው" ባሉት ሁኔታ "በአካባቢው በስፋት እየተተኮሰ ያለው ከባድ መሣሪያ ጥንታዊ ቅርሶች ላይም ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ፈጥሯል" ብለዋል።
ዛሬ ያነጋገርናቸው የላሊበላ ከተማ ነዋሪ ቅርሱ ላይ አንዳች ጉዳት ቢደርስበት፣ ሕዝቡም በየጊዜው እየደረሰበት ነው ላሉት ድርብርብ ችግር "ትናንት ከሕወሓት፣ ዛሬ ከብልጽግና ጋር ሆነው የሚሠሩ" ያሏቸው ሰዎች ተጠያቂ ናቸው ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።

አዉሮፕላን ማረፊያዉ በተደጋጋሚ ጥቃት ከደረሰባቸዉ አካባቢዎች አንዱ ነዉ
የላሊበላ አዉሮፕላን ማረፊያምስል AFP via Getty Images

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ