1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመናገር ነጻነት ወዴት?

ሐሙስ፣ ሰኔ 8 2015

ጋዜጠኞች ከስቱድዮ ጭምር እየታፈኑ የሚወሰዱበት፤ የታሰሩበት ሳይታወቅ በቤተሰብ እና በጠበቃ ሳይጎበኙና ፍርድቤት ሳይቀርቡ ለቀናት አስሮ መፍታት የተለመደ እየሆነ እንደሆነ ጋዜጠኞች በምሬት ይገልጻሉ።

https://p.dw.com/p/4SYhA
Ukraine Demonstration gegen Zensur und für Meinungsfreiheit in Kiew
ምስል SERGEI SUPINSKY/AFP/Getty Images

የመናገር ነጻነት ወዴት እየሄደ ነው

በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የሚደረገው እስርና ወከባ የፕረስ ነጻነትን የሚጋፋ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ሲሉ ጋዜጠኞች ተናገሩ። የተለያዩ ጋዜጠኞችና የሙያው ማሕበር አባላት ለDW እንደተናገሩት በሃገሪቱ የፕረስ ነጻነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነው። 
ወጣትዋ ጋዜጠኛ ያይኔ አበባ ግዛው የሃበሻ ወግ መጽሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ስትሆን በአለፈው ሚያዝያ ወር ከቤት ወጥታ ወደ ሥራ በተንቀሳቀሰችበት ወቅት በተለምዶ "22 ለም ሆቴል" በተባለ አካባቢ ዕንግዳ ነገር አጋጠማት።
"ሁለት ሰዎች ናቸው መንገድ ላይ እንደእገታም አትለውም፤ እንደ ጓደኛ ግራ እና ቀኝ ያዙኝ። ምንድነው ስል አንደኛው ሽጉጡንልጦ አሳየኝ። ከዛ እዛጋ ብወረጭም ዱላ ነው የሚደርስብኝ ብዬ በመፍራት V8 መኪና አዘጋጅተው ነበረ፤ መኪናቸው ውስች ገባሁኝ ከዛ ይዘውኝ ሄዱ።" 
ጋዜጠኛ ያይኔ አበባ ግዛው ለቡ ወደሚገኝ አንድ ጊዚያዊ እስርቤት ካስገቧት በኋላ ለ3 ቀናት ያለምግብ  እና ውሃ እንዳሰሯት አጫውታናለች። በታሰረችበት ወቅትም ከ3 ዓመታት በፊት በጋዜጣው በወጣ ጽሑፍ ላይ ተንተርሰው የኦሮሚያ ክልል ፕረዚደንትን እና የአዲስ አበባ ከንቲባን የሚወቅስ ጽሑፍ ጽፈሻል የሚል በእሷ አገላለጽ "ውሃ የማይቋጥር" ምርመራ ካደረጉባት በኋላ በሦስተኛው ቀን የሆነውን እንዲህ አወጋችን
"በ4 ኪሎ ብልጽግና እና ፓርላማ መሃል ወደ ስላሴ በሚያስገባው መንድ እሱ ጋር ውረጂ ቀጥ ብለሽ ሂጂ፤ታርጋ ይቀያይሩ ስለነበበረ እንዳላይባቸው ነው መሰለኝ፤ እኔም ፈርቼ ስለነበረ ፤ በሕይወት እተርፋለሁ የሚል እምነት አልነበረኝም ዞርሳልል ቀጥ ብዬ ሄድኩኝ። "
ጋዜጠኞች ከስቱድዮ ጭምር እየታፈኑ የሚወሰዱበት፤ የታሰሩበት ሳይታወቅ በቤተሰብ እና በጠበቃ ሳይጎበኙና ፍርድቤት ሳይቀርቡ ለቀናት አስሮ መፍታት የተለመደ እየሆነ እንደሆነ ጋዜጠኞች በምሬት ይገልጻሉ። ወጣቱ ጋዜጠኛ ቴድሮስ ካሳ ለ15 ዓመታት በሙያው አገልግሏል።
"በለውጡ ብዙ ተስፋ ነበረን ግን በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ወደኋላ ነው፤ ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፤በማንኛውም ጊዜ በማንኛውም ቦታ ሊታፈኑ ይችላሉ፤ የታሰሩበት ቦታ የት እንደሆነ አይታወቅም። የሚይዙአቸው ሰዎች ወደ ፍርድ ቤት የሚያቀርቡ አደሉም። እጅግ ኋላ ቀር የሆነ ጉዞ ላይ ነው ያለነው።"
  ጋዜጠኛ ቴድሮስ በጋዜጠኛው በኩልም የሙያውን ስነ ምግባር የሚያጎድፉ ተግባራት እንደሚንጸባረቁ ገልጿል።
ጋዜጠኛው የተጠናከረ ወጥ የሙያ ማሕበር ስላልመሰረተ ስለእስሩ እንኳን የሚጮሁለት የውጭ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪዎች እንደሆኑ አስተያየታቸውን ለDW የሰጡ ጋዜጠኞች ያስረዳሉ። ይህ ተደራጅቶ ለሙያው መብትና ለፕረስ ነጻነት የመታገል ጉዳይ ግን የራሱ የጋዜጠኛው ችግር እንደሆነ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዚደንት አንጋፋ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ አስረድቷል።
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ሃላፊዎችን አነጋግረን ነበር። በአስፈጻሚ አካላት የሚደረጉ እስሮችን በተመለከተ  ለባለስልጣኑ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን እና ሃላፊነት ውጭ መሆኑን ነግረውናል።

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር

ታምራት ዲንሳ