1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ርዕደ መሬት በዳውሮ ዞን

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2016

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ዛሬ ጠዋት የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ። የመሬት መንቀጥቀጡ ዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ የተከሰተው የዞኑ ዋና ከተማ ተርጫን ጨምሮ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ነው ።

https://p.dw.com/p/4fayY
የምድር ውስጣዊ ገጽታ ተምሳሌት
የምድር ውስጣዊ ገጽታ ተምሳሌት ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል agefotostock/IMAGO

የመሬት መንቀጥቀጥ በዳውሮ ዞን

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ዛሬ ጠዋት የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ። የመሬት መንቀጥቀጡ ዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ የተከሰተው የዞኑ ዋና ከተማ ተርጫን ጨምሮ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ነው ።

ጠዋት በግምት አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ከሁለት እስከ ሦስት ሰከንድ የሚደርስ ንዝረት መከሰቱን የተናገሩት ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች «በንዝረቱ የመኖሪያ ቤት ግድግዳዎችና የቤት ዕቃዎች ተንቀጥቅጠዋል ። አንዳንድ ነዋሪዎችም በድንጋጤ ከቤት በመውጣት ለመሮጥ ሲሞክሩ ተስተውለዋል » ብለዋል ። 

መጠነ ርዕደት

የመሬት መንቀጥቀጡ  መከሰቱን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ለማ መሠለ «ያም ሆኖ ንዝረቱ በነዋሪው ላይ ካስከተለው ጊዜያዊ መደናገጥ ውጭ በሰው ሕይወትም ሆነ ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አልተመዘገበም» ብለዋል ፡፡

የዳውሮ ዞን ውስጥ ከባድ ተሽከርካሪ የከሰል ማይዕድን ሲያመላልስ
የዳውሮ ዞን ውስጥ ከባድ ተሽከርካሪ የከሰል ማይዕድን ሲያመላልስ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Dawro zone government communications affairs

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ባለሞያና ተመራማሪ ዶክተር አታላይ አየለ ዛሬ ጠዋት አንድ ሰዓት ከሃያ አራት ደቂቃ ላይ በዳውሮ ዞን በሬክተር እስኬል 3 ነጥብ 0 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ተናግረዋል ፡፡

የእርግብግቢት ሥሜቱ ተርጫን ጨምሮ በሌሎች አጎራባች ከተሞች ቢከሰትም ዋናው የንዝረቱ ማዕከል ግን ከከተሞቹ እስከ 30 ኪሎ ሜትር በሚገመት ርቀት ላይ የተከሰተ መሆኑ የጠቀሱት ዶክተር አታላይ ይህም በሰው ሕይወትም ሆነ በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችልበት ደረጃው ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል  ፡፡

የሰምጥ ሸለቆ ሥጋት

የከርሰ-ምድር ድርብር ንጣፍ ገጽታ
የከርሰ-ምድር ድርብር ንጣፍ ገጽታ ። ርዕደ-መሬት የሚቀሰቀስበት ማዕከልምስል Wikipedia

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ባለሞያና ተመራማሪ ዶክተር አታላይ አየለ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ የመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭነት አለው ይላሉ ፡፡ በዚህ አካባቢ ለሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ከዓመታት በፊት በኮድ የተደገፈና ወጥ መመዘኛ ያለው መመሪያ መዘጋጁትን የጠቀሱት ባለሙያው " ይሁንእንጂ መመሪያው እስከአሁን ከወረቀት ባለፈ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም ፡፡ ምክንያቱም ግንባታውን የሚያከናውኑት የመንግሥትም ተቋማትም ሆኑ የግል ባለሀብቶች ተጨማሪ ወጪን የሚጠይቃቸው በመሆኑ ነው ፡፡ በእኛ አገር ሰው በቀላል ወጪ መገንባቱን ነው የሚያየው ፡፡ አካባቢው ለርዕደ መሬት የተጋለጠ በመሆኑ ክስተቱ ሊፈጠር ይችላል ፡፡ ይህ በሳይንስ የተረጋገጠ ነው " ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ