1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን አደጋ ላይ መሆናቸዉ ተገለፀ

ዓርብ፣ መስከረም 11 2016

በላሊበላና በአካባቢው ሰሞኑን በነበረው ጦርነት የከባድ ጦር መሣሪያ ተኩስ አካባቢው ላይ ባሉ ቅርሶች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ተገለፀ። በላሊበላ ከተማ በተለይም ብልብላ ጊዮርጊስ አካባቢ የነበሩ ጦርነቶችየከባድ መሳሪያ ድምፆች ንዝረት በአካባቢው ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችን ሳይጎዳ እንደማይቀር ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/4WhWf
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበዉ የላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያን
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበዉ የላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያን ምስል Annabelle Steffes-Halmer/DW

የላሊበላ ዉቅር አብያተክርስትያናት በጦርነቱ ለአደጋ ተጋልጠዋል

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በላሊበላና በአካባቢው ሰሞኑን በነበረው ጦርነት የከባድ ጦር መሣሪያ ተኩስ ንዝረት በአካባቢው ባሉ ታሪካዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፣ ጉዳዩ በባለሙያ እንዲረጋገጥም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞና ረቡዕ በላሊበላ ከተማ በተለይም ብልብላ ጊዮርጊስ አካባቢ የነበሩ ጦርነቶች የከባድ መሳሪያ ድምፆች ንዝረት በአካባቢው ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችን ሳይጎዳ እንደማይቀር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ 

ላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያናት
ላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያናት ምስል AFP via Getty Images


አንድ የላሊበላ ከተማ የቱሪዝም ባለሙያ በተለይ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ከባድ ማሳሪያዎች ከላሊበላ ከተማ  ወደ ብልብላ ጊዮርጊስ ሲተኮሱ ስለነበር በላሊበላ ከተማ የሚገኙት የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በነበረው ከፍተኛ ንዝርት ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ከላሊበላ ከተማ 32 ኪሎሜትር ላይ በሚገኘው ብልብላ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በወደቁ የከባድ ጦር መሣሪያ ድምፅ ንዝረት በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ጉዳቶች ሊደርሱ እንደሚችሉ አንድ የቤተክርስቲያናቱ አገልጋይ አመልክተዋል፡፡ ጉዳቱ በባለሙያ እንዲጠና የጠየቁት አገልጋዩ በነበረው ንዝረት ቀደም ሲል ጉዳት የነበረበት የቤተክርስቲያኑ ክፍል የተወሰነ ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስበት አይቀርም ነው ያሉት፡፡ የቱሪዝም ባለሙያው ስለ ብልባላ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲን ሁኔታ መረጃ እንደደረሳቸው አመልክተው ሆኖም ሄዶ ሁኔታውን ለማጣራት አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎት ባለመኖሩ ሊሳካልን አልቻለም፡፡ 


ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ