1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃይማኖት አስተማሪዎች እሥር

ሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2016

እናት ፓርቲ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና አገልጋዮቿ ላይ ይደርሳል ያለው "ማሳደድና እስር በአስቸኳይ" እንዲቆም ጠየቀ። ፓርቲው "ንቁ የሚባሉ" ያላቸው የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሶ ይህን መሰሉ ድርጊት እንዲቆም አሳስቧል።

https://p.dw.com/p/4fYW0
Enat Party – Logo – Oppositionspartei in Äthiopien
ምስል Enat Party

የሃይማኖት አስተማሪዎች እሥር

እናት ፓርቲ ከ"እምነት ዘመም" ፖለቲካ የሚመነጭ የሚመስል ያለው ተደጋጋሚ ዘመቻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ገዳማውያንና ምዕመናንን በከፋ ሁኔታ ተጠቂ ማድረጉን ገልጿል። 

የማሕበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ እና ዋና ፀሐፊ እንዲሁም ለተደጋጋሚ እሥር የተዳረጉ ያላቸው የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ሌሎችም "ንቁ የሚባሉ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች" በፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ቤታቸው መበርበሩን ማረጋገጡንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ምዕምናን ሰልፍ በፍራንክፈርት

ሁለቱ የማሕበረ ቅዱሳን የሥራ ኃላፊዎች ከአንድ ቀን እሥር በኋላ መለቀቃቸውን ያስታወቀው ፓርቲው በአንጻሩ የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መሪጌታ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ በእስር ላይ እንደሚገኙ በመግለጫው አመልክቷል። የሁለቱን ሰዎች መፈታት ማሕበረ ቅዱሳንም አረጋግጧል። ይህንኑ በተመለከተ የተጠየቁት የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰይፈ ስላሤ አያሌው መሰል ችግሮች ተደጋግመው መፈፀማቸውን አብራርተዋል።

የእናት ፓርቲ እና የመኢአድ ፕሬዝዳንቶች
የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰይፈ ስላሤ አያሌው (በፎቶው መሀል) የፍርሀት ድባብ ለመፍጠር ይደረጋል ያሉት ሩጫ እና ጫና ሊቆም ይገባል ብለዋል።ምስል Solomen Muche/DW

የሃይማኖት መሪዎቹ በምን ምክንያት እንደተያዙ እና ቀሪዎቹ እስካሁን ለምን እንዳልተለቀቁ የተጠየቁት የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄላን አብዲ ጉዳዩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱን የሚመለከት በመሆኑ ፌዴራል ፖሊስ አስተያየት ከመስጠት እንደሚቆጠብ አስታውቀዋል።

"እሱ ላይ እኛ አስተያየት መስጠት አንችልም"

መንግሥት "ለከት ካጣው" ሲል ከገለፀው የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት እጁን እንዲሰበሰብ ያስፈልጋል ያለው እናት ፓርቲ "ባልተገባ መንገድ የታሰሩ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና "በቤተ ክርስቲያን እና አባቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚያደርገውን ማሳደድና ሕገ ወጥ እስር በአስቸኳይ እንዲያቆም" ሲልም አሳስቧል።

እናት ፓርቲ የሰላም ስምምነቱ ለፓርላማ እንዲቀርብ ጠየቀ

በሌላ በኩል "ሃይማኖትን በመሳደብ እና ሕዝብን ለማጋጨት በማሴር" ተጠርጥሮ በፌዴራል ፖሊስ ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውሎ ለወራት በእሥር የቆየው በአስቂኝ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ይበልጥ የሚታወቀው ከያኒ ልጅ ያሬድ ወይም ያሬድ ዘላለምን ሰሞኑን መለቀቁ ተሰምቷል።

ግለሰቡ  አጸያፊ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አባቶችን፣ የእምነቱ ተከታዮችን እና የአምልኮ ቦታዎችን በማንቋሸሽ የተሳደበበት ቅጂ በማሕበራዊ መገናኛዎች መሰራጨቱም ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር