1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያዉያን በበርሊናለ የፌልም ፌስቲቫል ላይ ለምን ቀሩ?

ሐሙስ፣ የካቲት 14 2016

«ሐበሻ ቪው» በተሰኘዉ ድርጅት የኢትዮጵያን ፊልም በምዕራቡ ዓለም መድረክ እንዲቀርብ ጥረት በማድረጋቸዉ የሚታወቁት ወ/ሮ ትግስት ዳኘዉ በርሊናለ በተሰኘዉ በጀርመኑዓለም አቀፍ የፊልም ፊስቲቫል ላይ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ተሳታፊ ነበሩ። በመድረኩ ኢትዮጵያዉያን ባለሞያዎች አልነበሩም። መድረኩ ስለአፍሪቃ ፊልም እድገት እየተሰራ መሆኑ የታየበት ነዉ።

https://p.dw.com/p/4cm3S
74 ተኛዉ በርሊናለ - የጀርመን ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል
74 ተኛዉ በርሊናለ - የጀርመን ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ምስል Markus Schreiber/AP/picture alliance

በወቅታዊ ሁኔታ እና በቪዛ ችግር ኢትዮጵያዉያን በ 74ኛዉ በበርሊናለ ፊልም ፌስቲቫል ላይ አልተገኙም

የካቲት ሰባት ምሽት የጀመረዉና እሁድ የካቲት 17 ቀን  2016 ዓ.ም በሚጠናቀቀዉ በጀርመኑ ዓለም አቀፍ የፊልም ፊስቲቫል በርሊናለ ላይ ያገኘናቸዉ እና «ሐበሻ ቪው» የተሰኘዉ ድርጅት በኩል የኢትዮጵያን ፊልም በተለይ በምዕራቡ ዓለም ፊልም መድረክ እንዲቀርብ ጥረት በማድረጋቸዉ የሚታወቁት  ወ/ሮ ትግስት ዳኘዉ ከበደ ብቸኛዋ ተሳታፊ ኢትዮጵያዊ ናቸዉ። «ሐበሻ ቪው» የተሰኘዉ የኢትዮጵያን ፊልሞች የሚያስተዋዉቀዉ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትእግስት ዳኘዉ ከበደ፤ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዉያን የተሰሩ ፊልሞችን ወደ አዉሮጳ በማምጣትና በማስተዋወቅ የኢትዮጵያዉያን ፊልሞች በዓለም አቀፉ የፊልም መድረክ ተፈላጊነትን እንዲያገኙ ጥረት ሲያደርጉ ዓመታትን አስቆጠረዋል። ወ/ሮ ትግስት በጀርመንዋ መዲና በሚካሄድ ላይ ባለዉ በዓለም አቀፉ ዓመታዊ የፊልም ፌስቲቫል »በርሊናለ» ላይ ሦስት ቀናት የተለያዩ ስብሰባዎችን እና ዉይይቶችን አካሂደዋል። ወ/ሮ ትግስት እንደነገሩን ዘንድሮ በበርሊናለ ዓለም አቀፉ የፊልም ፌስቲቫል ላይ በኢትዮጵያዉያን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተሰራን ፊልም አልቀረበም።

 

 

ወ/ሮ ትግስት ዘንድሮ በበርሊናለ ዓለም አቀፉ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የተጋበዙት ስለኢትዮጵያ ብሎም በአጠቃላይ ስለ አፍሪቃ የፊልም ስራ እና ኢንዱስትሪዉ ላይ የተለያዩ  ዉይይቶችን እና ልምዶችን ለመለዋወጥ ነዉ። ይሁን እና ዘንድሮም ሆነ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያዉያን የፊልም ሰራተኞች ለጉዞ የሚሆናቸዉን የይለፍ ቪዛን የማግኘት ችግር ስለገጠማቸዉ በፊስቲቫሉ ላይ አለመገኘታቸዉ ተመልክቷል። ወ/ሮ ትግስት እንደነገሩን ቀደም ባሉ ዓመታት በርሊናለ ላይ የፊልም ባለሞያዎች በኢትዮጵያዉያን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተሰሩ አጫጭር ፊልሞችን ይዘዉ ይቀርቡ ነበር።

 ወ/ሮ ትእግስት ዳኘዉ ከበደ፤ «ሐበሻ ቪው» የስራ አስኪያጅ
ወ/ሮ ትእግስት ዳኘዉ ከበደ፤ «ሐበሻ ቪው» የስራ አስኪያጅምስል Habeshaview

 

 

በዘንድሮው የበርሊኑ ፊልም ፌስቲቫል ላይ አስር ​​የአፍሪቃ ፊልሞችለእይታ ቀርበዋል። ኬንያዊቷ የኦስካር ተሸላሚ ተዋናይ እና ፊልም ተዋናይ ሉፒታ ንዮንግኦ የዘንድሮውን የበርሊን ፊልም ፌስቲቫል በዳኝነት ትመራለች። ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት እንዲሁም ዘንድሮ ጀርመን መዲና ላይ በሚዘጋጀዉ ዓለምአቀፉ የፊልም ፌስቲቫል በርሊናለ ላይ ሊገኙ የቻሉት በአዉሮጳ የፌልም ግብይት ድርጅት በኩል ተጋብዘዉ እንደሆነ ወ/ሮ ትግስት ነግረዉናል። ወ/ሮ ትግስት በተሳተፉባቸዉ የዉይይት መድረኮች በርካታ አፍሪቃዉያን የፊልም ሰራተኞችን ተዋዉቀዋል። ወ/ሮ  ትግስት እንደነገሩን፣ በዚህ ዓመት በርካታ አፍሪቃውያን ፊልም ሰሪዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁጥር ብዛት በበርሊናሌ የፊልም ፌስቲቫል ላይ እየተሳተፉ ነው። ትግስትን ጨምሮ ከ400 በላይ የአፍሪቃ የፊልም ባለሙያዎች በበርሊናሌ በተዘጋጁ የተለያዩ ኮንፈረንሶች እና የፓናል ውይይቶች ላይ ይገኛሉ።

ሉፒታ ንዮንግኦ፤ ኬንያዊቷ የኦስካር ተሸላሚ ተዋናይ እና ፊልም ተዋናይ  የዘንድሮውን የበርሊን ፊልም ፌስቲቫል ላይ ዳኛ ናት
ሉፒታ ንዮንግኦ፤ ኬንያዊቷ የኦስካር ተሸላሚ ተዋናይ እና ፊልም ተዋናይ የዘንድሮውን የበርሊን ፊልም ፌስቲቫል ላይ ዳኛ ናትምስል K.M. Krause/picture alliance

አፍርክሲም ባንክ በመባል የሚታወቀዉ የአፍሪቃ አስመጪና ላኪ ባንክ በያዝነዉ የጎርጎረሳዉን 2024 ዓመት የአፍሪቃን ፊልም ኢንዱስትሪ ለማጎልበት የ 1 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ መመደቡን ያስታወቀዉ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት 2023 መጠናቀቅያ ላይ ነበር።  የአፍሪቃ የፊልም ኢንዱስትሪ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የመቀጠር አቅም ቢኖረውም፣ በአህጉሪቱ በሚታየዉ የባለቤትነት መብት ሕጎች ደካማነት፣ በአሠራር አፈጻጸም እና በግንዛቤ ጉድለት ሳቢያ፤ የገንዘብ ድጋፍ እጢት እንዲሁም የባለቤትነት መብት ጥሰትን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች ተደቅነውበት ይታያል። የአፍሪቃ የፊልም ኢንዱስትሪ የመሰረተ ልማትና የቴክኖሎጂ ክፍተት፣ የአቅም እጥረት፣ ችሎታ ያላቸዉ  ባለሙያዎች እጥረት፣ እንዲሁም ወደ ዓለም አቀፉ ገበያ ለመግባት ውስን መንገድ በማግኘቱ የአፍሪቃ ፈጠራና ባህላዊ ምርቶች ብዙውን ጊዜ ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ  ለመድረስ መቸገራቸዉን የበርሊናለዉ የፊልም ፌስቲቫል መወያያ መድረክ ዋና ርእስ እንደነበር ወ/ሮ ትግስት ነግረዉናል። 

74 ተኛዉ በርሊናለ - የጀርመን ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል
74 ተኛዉ በርሊናለ - የጀርመን ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ምስል Azadeh Karimi/DW

ወ/ሮ  ትግስት በአፍሪቃ ጠንካራ የፊልም ኢንዱስትሪ ያላት ናይጀርያ እንደሆነች ተናግረዋል። በመከተል ደቡብ አፍሪቃ ከአፍሪቃ በርካታ ፊልሞችን በመስራት ከናይጀርያ ተከትላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በሦስተኛ ደረጃ ኬንያ የፊልም አምራች አገር ናት። በአሁኑ ወቅት በአፍሪቃ የፊልምና የቪድዮ ኢንዱስትሪዎች በአህጉሪቱ ዓመታዊ ገቢ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ እና በግምት አምስት ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ በዘርፉ እየሰራ እንደሆን የወጡ ጥናታዊ ዘገባዎች ያሳያሉ።

«ሐበሻ ቪው» የተሰኘዉ የኢትዮጵያንን ፊልሞች ወደ አዉሮጳበማምጣት የሚያስተዋዉቀዉ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትግስት ዳኘዉ፤ ከበርሊናለ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል በርካታ እዉቀቶችን ይዘዉ እንደሚመለሱ ተናግረዋል። ከዞህ ሌላ  የታቀደዉ የአፍሪቃ ፊልም ስራ ማጎልበቻ ድጋፍ መልስን ከወራቶች በኋላ ይሰማል ብለዉ ተስፋ እንደሚad,ርጉም ተናግረዋል።   

በፊስቲቫሉ በአሸናፊነት የተመረጠዉ ፊልም ወርቅማዉን ድብ «ጎልድነ ቤር» ያገኛል
በፊስቲቫሉ በአሸናፊነት የተመረጠዉ ፊልም ወርቅማዉን ድብ «ጎልድነ ቤር» ያገኛል ምስል Jens Kalaene/dpa/picture alliance

ፖለቲካ ፋሽን፣ ኪነ-ጥበብ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰባዊ ኹነቶች በፊልም፣ በዉይይት መድረክ እና በአዉደ ርዕይ ለ10 ቀናት የሚቀርብበት የበርሊኑ የፊልም ፊስቲቫል በርሊናለ የተለያዩ ሽልማቶች እና እዉቅናዎችን እየሰጠ እንደቀጠለ ነዉ።  በፊስቲቫሉ በሚጠቃለልበት እለት  ወርቅማዉን ድብ ጎልድነ ቤር አሸናፊዉ የትኛዉ ፊልም እና በማን የተሰራዉ ነዉ የሚለዉ ጥያቄ መልስ  በጉጉት እየተጠበቀ ነዉ። የሐበሻ ቪው ስራ አስኪያጅ፣ ወ/ሮ ትግስት ዳኘዉ ከበደ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉዉን የድምፅ ቅንብር እንዲad,ምጡ እንጋብዛለን

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ