1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ብርቱ የበጀት ጉድለት ገጥሟታል

ሐሙስ፣ ሰኔ 1 2015

ለ2016 በጀት ዓመት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው 801 ቢሊየን ብር ካለፉት ዓመታት በጀት አንፃር የልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት በቂ አለመሆኑ ተገልጿል ። መንግሥት ከሀገር ውስጥ ገቢ እና ከውጪ አገር ርዳታ ምንጮች 520 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገልጸዋል ።

https://p.dw.com/p/4SLSi
Äthiopien Parlament Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

በጀቱ የአምናውን ለመስተካከል 40% ጭማሪ ያሻዋል፦ ባለሞያ

ለ2016 በጀት ዓመት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው 801 ቢሊየን ብር ካለፉት ዓመታት በጀት አንፃር የልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት በቂ አለመሆኑ ተገልጿል ። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ዛሬ የበጀት መግለጫውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ይህንኑ ተናግረዋል።  መንግሥት ከሀገር ውስጥ ገቢ እና ከውጪ አገር ርዳታ ምንጮች 520 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል ። በታቀደው ገቢ እና ወጪ መካከል ግን የ281 ቢሊየን ብር የበጀት ጉድለት መኖሩን አልሸሸጉም ። ይህ ጉድለትም ከውጭ ሀገር 39 ቢሊዮን ብር ቀሪው ደግሞ ከሀገር ውስጥ በብድር እንዲሸፈን መታቀዱን ተናግረዋል። ጉድለቱን ለመሸፈን ከታቀደው ብድር ደግሞ 53 ቢሊዮን ግድም ብሩ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ዋና ብድር ክፍያየሚውል ነው ተብሏል ። 

ባለፉት ዓመታት የተከሰቱ ተደራራቢ ቀውሶች የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ያስታወቁት የገንዘብ ሚኒስትሩ እንዲያም ሆኖ ግን ኢኮኖሚው በ6.1 በመቶ ማደጉንና በ2016 ደግሞ በ7.5 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመት ገልፀዋል። ሚኒስትሩ አክለውም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የወደሙ ንብረቶች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ዜጎችን ለማቋቋም ከመንግሥት ግምጃ ቤት 20 ቢሊዮን ብር መመደቡን አብራርተዋል። ያነጋገርናቸው አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ደግሞ መንግሥት ለዓመቱ የያዘው በጀት ከዋጋ ግሽበት አንፃር ካለፈው ዓመት ዝቅ ያል ነው ብለዋል። ከአምናው በጀት በ1.9 በመቶ ብቻ ሳይሆን ይህንን ግሽበት ለማካካስ እስከ 40 በመቶ የበጀት ጭማሪ ማድረግ ይጠበቅበትም እንደናበርም ገልፀዋል።

801.65 ሆኖ የቀረበው በጀት "የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጐችን ከመርዳት፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ከማቋቋም፣ በቀጣይ ሊኖሩ የሚችሉን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ለውጥ ዓላማዎችን ከማሳካት አንፃር የተቃኘ" ነው ተብሎለታ። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ዛሬ ለተወካዮች ምክር ቤት ዝርዝሩን ሲያቀርቡ እንዳሉት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቀውስ ተፈትኗል። በዋናነት በሀገር ውስጥ ገቢ ይሸፈናል የተባለው በጀት ለሀገር መከላከያ የሚመደበው ካለፈው አመት አንፃር መጠኑ ዝቅ እንደሚል፣ በጀቱ ካለፈው ዓመት ሲተያይ የልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት በቂ እንደማይሆን በዚህም ምክንያት መንግሥት አዳዲስ ቅጥር እንደማይፈጽም አብራርተዋል። በጀቱ የ 281.05 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንደሚኖረውም ገልፀዋል።

አንዳንድ ተንታኞች የበጀት ክፍተቱ በተንሰራፋው የኑሮ ውድነት ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው ይላሉ
አንዳንድ ተንታኞች የበጀት ክፍተቱ በተንሰራፋው የኑሮ ውድነት ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው ይላሉምስል Seyoum Getu/DW

ለፌደራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች 369.6 ቢሊየን ብር ፣ ለካፒታል ወጪዎች 203.9 ቢሊየን ብር ፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 214.07 ቢሊየን ብር እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 14 ቢሊየን በጠቅላላው 801.65 ቢሊየን ሆኖ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ በጀቱ የዋጋ ንረትን ለሚያረጋጉ ጉዳዮችም ትኩረት የተሰጠው ነው ተብሏል። ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ግን መንግሥት ይህንን ግሽበት ለማካካስ እስከ 40 በመቶ የበጀት ጭማሪ ማድረግሲጠበቅበት ካምናው አንፃር የ 1.9 በመቶ ብቻ ጭማሪ ማድረገጉን ተችተዋል። 

መንግሥት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የወደሙ ንብረቶች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ዜጎችን ለማቋቋም ከመንግሥት ግምጃ ቤት 20 ቢሊዮን ብር መድቧል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ደግዬ ዓለሙ እንደሚሉት ግን ከደረሰው ውድመት አንፃግ ይህ ዝቅተኛ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በበጀቱ ላይ በርከት ያሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ምክር ቤቱ በጀቱ ላይ ለአንድ ወር ከተወያየበት በኋላ የሪፐብሊኩ ጠቅላይ ሚኒስትር በተገኙበት ወደፊት ያፀድቀዋል። 

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሀመድ