1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሙያው የተከፈለ መስዋዕትነት

ዓርብ፣ የካቲት 29 2016

"ወረፋ ከያዙት ባጃጆች በአንዱ ለመሳፈር ስንፈልግ ከወረፋ ውጭ የነበረ ባለባጃጅ እኔ ጋር ካልገባችሁ ብሎ በግድ ወተወተን። እኔ ሰውነቴ ቅፍፍ እያለኝ ነበር የገባሁት። ትንሽ እንደተጓዝን ሾፌሩ ዘሎ በመውረድ እኛን ከአንድ ሞተር ብስክሌት ጋር አጋጨን"

https://p.dw.com/p/4dEaE
Journalist Ephrem Beyene
ምስል Private

ለተሽከርካሪ ወንበር የዳረገው ፈተና

የጋዜጠኝነት ጅማሬ

ብዙው አዳጊ ኢትዮጵያዊ አድገህ ምን ትሆናለህ? ሲባል በወቅቱ ለኪስ ከፍተኛ ገቢና በማሕበረሰቡ ዘንድ ደግሞ ከፍተኛ ክብር ያሰጣሉ ተብለው የሚነገርላቸው ዶክተር፣ ፓይለት፣ ወዘተ ማለት ዝውቱር ነበረ። የያኔው ተማሪ የአሁኑ ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ግን ምርጫው ጋዜጠኝነት ነበረ። ሕልሙ ተሳክቶለት በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ከተመረቀ በኋላ አሃዱ ብሎ ወደ ሥራ አለም እንደገባ አጫውቶናል።

`` ከባድ ጊዜ ነበረ። በወቅቱ ከ97 ዓም በኋላ ብዙ ጋዜጦች የተዘጉበት፤ ብዙ ሚድያዎች ፍቃድ የተነጠቁበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ ነጋድራስ ጋዜጣ ላይ ስቀጠር ካርቱኖችን ስሰራ ነበረ፤ ከዛ ቀስ እያልኩኝ ዜና ነበር ስሰራ የነበረው።``

ሙያዊ አስተዋጽኦው

ወጣቱ ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ በነጋድራስና ሰንደቅ የተለያዩ ዓምዶችን በመስራት ከቆየ በኋላ አብረው ይሰሩ ከነበሩት ጋዜጠኞች ጋር ``ኢትዮምህዳር`` የምትል ጋዜጣ በማቋቋም የጋዜጠኝነት ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህ ሂደት ስላበረከታቸው አስተዋጽኦዎች በጥቂቱ እንዲህ ይገልጸዋል።

`` በፊት እሰራበት በነበረው ነጋድራስ ጋዜጣ ላይ አተኩር የነበረው ኢኮኖኒ ላይ፤ ወጣቶችን በማበረታታት ላይ ነበር። ያልታወቁ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን በማስተዋወቅ ላይ ነበር ብዙ ጊዜ ስሰራ የነበረው። የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ  ለመጀመሪያ ጊዜ ሚድያ ላይ ያወጣሁት እኔ ነበርኩ። ከዛ በሰንደቅና ኢትዮ ምህዳር ቆይታዬ በምርመራዊ ጋዜጠኝነት ላይ አተኩር ነበር። ከሙስና ጋር የተያያዙ ትንሽ ጠንከር ያሉ ዜናዎችን እሰራ ነበር።``

ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ጉዳት ሳይደርስበት በፊት
ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ጉዳት ሳይደርስበት በፊትምስል Private

ለተሽከርካሪ ወንበር የዳረገው ፈተና

ጋዜጠኛ ኤፍሬም በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ቆይታው ብዙዎች የማይደፍሩትን ከደፈሩትም እስርና ግድያም ሊያስከትል የሚችለውን የምርመራ ጋዜጠኝነትን ምርጫው አድርጓል። በወቅቱ አንድ የሙስና መረጃ ከታማኝ ምንጭ አግኝቶ ዱካውን ተከታትሎ ለውጤት ማብቃቱን ይገልጻል። በሐዋሳ ከተማ የሚገኝ አንድ የፌደራል መንግስት ተቋም የተፈጸመ ሙስና የሚያጋልጥ ሪፖርቱም በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ለንባብ አበቃ። የተፈራው አልቀረም፤ ጋዜጣው አድራሻው በአዲስ አበባ ቢሆንም በሃዋሳ ክስ ተመሰረተበት፤ እሱም ጋዜጣውም።

በቀጠሮ ቀን የጋዜጣው ዋና ሥራአስኪያጅ ጌታቸው ወርቁ፣ ጋዜጠኛ ሚልዮንና ኤፍሬም በቀጠሮአቸው መሰረት ፍርድቤት ተገኙ። ግን የጠበቁት አልጠበቃቸውም። እኛ ባልተሳተፍንበት ችሎት ``የእናንተ ጉዳይ ለከሰአት ተቅጥሯል`` ተባልን በማለት አጫወተን። በዚሁ ጊዜ ጊዚያቸውን ለመጠቀም አንዳንድ ለጋዜጣው የሚሆኑ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ተስማምተው በባለ 3 እግር ባጃጅ ለመሄድ እግራቸውን አነሱ። ከዚያስ

``` እኛ ለከከዓት ስለተቀጠረ ለጋዜጣችን የሚሆኑ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ወስነን በባለ 3 እግር ታክሲ ለመሄድ ተንቀሳቀስን። ወረፋ ከያዙት በአንዱ ለመሳፈር ስንፈልግ ከወረፋ ውጭ የነበረ ባለባጃጅ እኔ ጋር ካልገባችሁ ብሎ በግድ ወተወተን። እኔ ሰውነቴ ቅፍፍ እያለኝ ነበር የገባሁት። ትንሽ እንደተጓዝን ታክሲውን ከሚገባ በላይ ያፈጥነው ስለነበረ እኔና ግታቸው ወርቁ አቁመው! አውርደን እያልን መጮሕ ጀመርን። ከዚያ ሾፌሩ ዘሎ በመውረድ እኛን ከአንድ ሞተር ብስክሌት ጋር አጋጨን``

የባለ 3 እግር ታክሲው  ሾፍር እነሱን ከሞተር ብስክሌት ጋር ካጋጫቸው በኋላ ዘሎ በሰላም ሲወድ 3ቱ ጋዜጠኞች ግን በባለ 3 እግር ታክሲዋ 3 ጊዜ ተገለባብጠው ወደቁ። ከዚያ የሆንኩትን አላውቅም ይላል ጋዜጠኛ ኤፍሬም።

ጛዜጠኛ ኤፍሬም በየነ የአካል ጉዳት ከደረሰበት በኋላ የሙያ አጋሮቹ ሲያጽናኑት
ጛዜጠኛ ኤፍሬም በየነ የአካል ጉዳት ከደረሰበት በኋላ የሙያ አጋሮቹ ሲያጽናኑትምስል Private

ጋዜጠኛ ጌታቸውና ሚልዮን የደረሰባቸው ጉዳት ለክፉ ባይሰጥም ጋዜጠኛ ኤፍሬም ግን ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት አጫውቶናል። ጋዜጠኛው ሙስናን የሚያጋልጡ የምርመራ ዘገባዎች ይጽፉ የነበሩ እጆቹ ብእር አደለም እንጀራ ጠቅልለው መጉረስ አይችሉም። ወዲያ ወዲህ ተሯሩጦ የሚዘግብባቸው እግሮቹ አሁን በተሽከርካሪ ወንበር ካልሆነ በጀ ብለው አይራመዱም።

በዕንቅርት ላይ ጀሮደግፍም ደርሶብኛል ይላል ጋዜጠኛ ኤፍሬም። በህክምና በተፈጸመ ስህተት ሌላ በሽታ፤ ሌላ ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ስቃይ እንዳጋጠመው ነግሮናል።

በ``ስም አጥፍታችኋል`` ክሱም አብሮት እንደ ድርጅት የተከሰሰ፤ አደጋው ሲደርስም አብሮት የነበረ የጋዜጣው ዋና መስራችና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ግታቸው ወርቁ ጋዜጠኛ ኤፍሬምን ``ለሙያው ሲል በለጋ ዕድሜው ከባድ መስዋዕትነት የከፈለ ጋዜጠኛ`` ሲል ይገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ይገደላሉ፣ አለፍርድ ይታሰራሉ፣ ከመንግስት ባለስልጣናትም መረጃ የማግኘት ነጻነታቸው አብዝተው ይከለከላሉ ሲሉ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ይወቅሳሉ። በመሆኑም በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሥራ ከባድና ፈታኝ አድርገውታል። ወጣቱ ጋዜጠኛ ኤፍሬም ግን ወጣት ጋዜጠኞች ለሙያቸው ያላቸውን ታማኝነት ማሳየት አለባቸው ይላል።

አሁን ለሕክምና በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ የሚገኘው ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ከተሽከርካሪ ወንበር ወርዶ አሁንም ሕዝቡን ለማገልገል ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። ጤናው ወደ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቀው የገለጸው ጋዜጠኛው ይህ በሱ አቅም የሚሸፈን እንዳልሆነ ነግሮናል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ነጋሽ መሐመድ