1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢመሪተስ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ ፤አንጋፋው የጂኦቴክኒካል ተመራማሪ

ረቡዕ፣ ግንቦት 30 2015

አንጋፋው የጂኦቴክኒካል ምህንድስና ባለሙያ ኢመሪተስ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ በኢትዮጵ ጅኦቴክኒካል ምህንድስና ዘርፍ የራሳቸውን አሻራ ያስቀመጡ ተመራማሪ ናቸው። ፕሮፌሰሩ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተቋም በማስተማር እና በምርምር ስራ ከ35 አመታት በላይ ሰርተዋል።

https://p.dw.com/p/4SGxx
Äthiopien Alemayehu Tefera
ምስል Privat

የኢመሬተስ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፋራ የሙያ ጉዞ

 
የኢትዮጵያ ጂኦቴክኒካል ሶሳይቲ  በቅርቡ በዘርፉ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ  ለአንጋፋው የጂኦቴክኒካል ምህንድስና ባለሙያ  ኢመሪተስ  ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ እውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም እኝህን አንጋፋ የሳይንስ ሰው ያስተዋውቃል። 
አንጋፋው  የጂኦቴክኒካል ምህንድስና ባለሙያ  ኢመሪተስ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ በኢትዮጵ ጅኦቴክኒካል ምህንድስና ዘርፍ የራሳቸውን የማይደበዝዝ አሻራ ያስቀመጡ ተመራማሪ ናቸው። ፕሮፌሰሩ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተቋም በማስተማር እና በምርምር ስራ ከ35 አመታት በላይ ሰርተዋል።የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የምህንድስና እና የቴክኖሎጂ ቡድን ሊቀመንበር፣ መስራች  እና የቦርድ አባልም ናቸው። ኢመሪተስ ፕሮፌሰር አለማየሁ  የተወለዱት  ከመዲናይቱ አዲስ አበባ  በቅርብ ርቀት በምትገኘው  በረህ በምትባል ወረዳ  ሲሆን ያደጉት ግን አዲስ አበባ ነው።
በዚያን ዘመን እንደነበረው አብዛኛው ኢትጵያዊ  ፊደል የቆጠሩት ቄስ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አዲስ አበባ በሚገኘው የኮከበ ፅባህ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
ፕሮፌሰሩ ረጅሙን የሙያ ጉዞ የጀመሩት ከቀድሞው የአዲስ አበባ  ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ ከአሁኑ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በመረጡት  የሲቪል ምህንድስና  ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በመያዝ ነው።
በ1953 ዓ/ም  በሲቪል ምህንድስና ከተመረቁ በኋላም ለሁለተኛ ዲግሪያቸው ከእስራኤል መንግሥት ነፃ የትምህርት ዕድል  አገኙ። በወቅቱ ከኢትዮጵያ ለመውጣት ቢያቅማሙም በመጨረሻ ግን ዕድሉን በመጠቀም በእስራኤል ሀገር ሃይፋ በሚገኘው ቴክኒዮን በተባለ የቴክኖሎጂ ተቋም ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ።
በዚህ ሁኔታ ትምህርታቸውን በእብራይስጥ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመከታተል በየሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በጆኦቴክኒካል ምህንድስና አጠናቀዋል። በኋላም በዚሁ ዩንቨርሲቲ በረዳት መምህርነት በመስርራት ጥሩ ልምድ አግኝተዋል።በቀሰሙት ልምድ እና ዕውቀት ሀገራቸውን ለማገልገል በ1957 ዓ/ም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።እንደተመለሱም በምህንድስና ኮሌጅ ውስጥ እስከ 1959 መጨረሻ ያስተማሩ ሲሆን፤ ቆይተውም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የጅኦሎጂ የትምህርት ክፍልን ተቀላቅለዋል።
በዚህ ወቅት የዛሬውን  ኢመሪተስ  ፕሮፈሰር የያኔውን ወጣት አለማየሁን  ቀለም ገብነት የተረዱት በዚያን ጊዜ  የነበሩት እስራኤላዊው የኮሌጁ  ሃላፊ  ታዲያ  የዶክትሬት ዲግሪ እንዲማሩ መወትወታቸውን ቀጠሉ። እሳቸውም ምክሩን ተቀብለው ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመያዝ በ1960 ዓ/ም ወደ ጀርመን ሀገር ከባለቤታቸው ጋር  አቀኑ። የዶክትሬት ተማሪ ሆነው ከመመዝገባቸው በፊት ግን ለስድስት ወራት  የጀርመንኛ ቋንቋ ትምህርትን ተከታትለዋል።
ምንም እንኳ መጀመሪያ አካባቢ ይህ መሰሉ ችግር ቢገጥማቸውም ውለው ሲያድሩ ግን ጀርመኖቹ ብቻ በሚሰሩት የዩንቨርሲቲው የምርምር ስራ ጭምር መሳተፍ ችለዋል።
በዚህ ሁኔታ በዚህ ሁኔታ የጀርመን የከፍተኛ ትምህርት ልውውጥ አገልግሎት  በጀርመንኛው ምህፃሩ/DAAD/በሰጣቸው የትምህርት ዕድል ከያኔው ምዕራብ ጀርመን አኸን የቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ በ1966 ዓ/ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።ቋንቋውን እና የምህንድስና ሳይንሱን አጣምረው የተማሩት ፕሮፌሰር አለማየሁ ለተቋሙ በጀርመንኛ ቋንቋ የምርምር  ጽሁፎችንም አበርክተዋል።እስከ 1967 ዓ/ም ድረስም በጀርመን ሀገር በዚሁ ዩንቨርሲቲ  «ሳይንቲፊክ አሶሸት» የሚል ማዕረግ ተሰጥቷቸው በማስተማር ስራ ቆይተዋል።ምንም እንኳ ስራው የሚወዱት እና ጥሩ ክፍያ  የሚያስገኝ ቢሆንም በኢትዮጵያ ወቅቱ የአብዮት እና  የለውጥ ጊዜ በመሆኑ፤ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ስር የእድገት በህብረት ዘመቻን ተቀላቀሉ።
ከዘጠኝ  የአገልግሎት ወራት በኋላም በዩንቨርሲቲው የማስተማር ስራቸውን ቀጥለዋል።በኢትዮጵያ የጂኦቴክኒካል ምህንድስና የትምህርት አባት ተደርገው የሚቆጠሩት ኢመሪተስ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ፤በወቅቱ በነበረው የኮንስትራክሽን ሚንስቴር መስሪያ ቤት የኮሚቴ አባል በመሆን የጀርመንን የግንባታ መመሪያ መሰረት በማድረግ  በ1975 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የግንባታ ስራ መመሪያ/Construction Code/ አዘጋጅተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በመወከል የዩኔስኮ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል ሆነው  በመመረጥም ድርጅቱን በሙያቸው አገልግለዋል።በ1983 ዓ/ም ደግሞ በሚያስተምሩበት  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው የተመረጡ ፕሬዝዳንት ሆነው ሰርተዋል። ነገር ግን በተመረጡ በዓመቱ  የመንግስትን የአካዳሚክ ነፃነት መጣስ እና የተማሪዎችን  እስር በመቃወማቸው  ብዙም ሳይቆዩ ለዕስር ተዳርገዋል።
1984 እስከ 1995 ዓ/ም ድረስ ከአስር አመታት በላይ በእስር  ከቆዩ በኋላ  በ1996 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ወደ ዩንቨርስቲው የተመለሱት  ፕሮፌሰሩ፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው እና እስር ቤት በቆዩባቸው አመታት ጭምር በምህንድስና ሳይንስ ላይ  ያተኮሩ አምስት መፅሃፍትን ያዘጋጁ ሲሆን አንዳንዶቹም አሁንም ድረስ ለመማሪያነት ያገለግላሉ። በሙያው በቆዩባቸው ዓመታት ርዕደ መሬትን ፣ በሞቃታማ የአፈር ባህሪያትን እና መሬት መንሸራተትን በመሳሰሉ ጉዳዮች  በርካታ  ምርምሮችን በማድረግ በሃገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ መጽሔቶች አሳትመዋል።  
ለዚህ የላቀ አገልግሎታቸውም በጎርጎሪያኑ 2016 ዓ/ም ጡረታ ሲወጡ ዩንቨርሲቲው ኢመሪተስ የሚል የክብር ማዕረግ የሰጣቸው ሲሆን፤ አሁንም ድረስ በዩንቨርሲቲው በማማከር ስራ ላይ እና ይገኛሉ።

Äthiopien Alemayehu Tefera
ምስል Privat
Hochschulen - Hauptgebäude der RWTH in Aachen
ምስል picture-alliance/dpa
Äthiopien Alemayehu Tefera
ምስል Privat
Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU
ምስል DW

40 ለሚጠጉ ዓመታት በዘርፉ ላደረጉት አስተዋፅኦም በ2022 ዓ/ም የተመሰረተው ጂኦቴክኒካል ሶሳይቲ የተባለው የሙያ ማህበርም በቅርቡ እውቅና እና ሽልማት ሰጥቷቸዋል።ማህበሩ በየዓመቱ በሚያካሂዳቸው አመታዊ ስብሰባዎች ላይም በስማቸው ጥናቶችን ለማቅረብ ወስኗል።
በረጅሙ የሙያ ጉዟቸው ጥልቅ የሀገር  እና የሙያ ፍቅር እንደነበራቸው የገለፁት ኢመሪተስ ፕሮፌሰሩ ወጣቱ ትውልድም ይህንን  ፈለግ ቢከተል መልካም መሆኑን መክረዋል።ኢመሪተስ  ፕሮፌሰር አለማየሁ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በዩንቨርሲቲው የማስተማር ስራቸውን ቢያቆሙም በዘርፉ በርካታ ባለሙያዎች በእግራቸው እንዲተኩ አድርገዋል።በዚህም ደስታቸው ወደር የለውም።
ለቃለ መጠይቁ ኢመሪተስ  ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራን እያመሰገንን፤ ሶስት አስርተ አመታትን በተሻገረው የምህንድስና ሳይንስ አበርክቷቸው  ላይ ያተኮረው የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በዚህ ተጠናቋል። 

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ