1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች ሮሮ

ሐሙስ፣ መጋቢት 22 2014

ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖችና ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሰፈሩ ተፈናቃዮች ለምግብ እና መጠለያ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ። እንደ ተፈናቃዮቹ ርዳታ ካገኙ 2 ወራት አልፏቸዋል።  

https://p.dw.com/p/49IWh
Äthiopien | Binnenvertriebene in Oromia
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በክልሉ ከ2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃይ እንዳለ ይነገራል

ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖችና ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሰፈሩ ተፈናቃዮች ለምግብ እና መጠለያ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ። እንደ ተፈናቃዮቹ እርዳታ ካገኙ 2 ወራት አልፏቸዋል።  ከ60 ዓመት በላይ ለሆናቸው 10 ያህል ተፈናቃዮች መንግስት ከትናንት በስትያ በሐይቅ መጠለያ ጣቢያ እስከ 15 ኪሎ ስንዴ ስጥቶ እንደተመለሰም ተናግረዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ከ34 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በዞኑ እንደሚገኙ አመላክተው ስምንት ሺህ ያህሉ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጠዋል። የምግብ አቅርቦቱ ላይ በተሟላ መንገድ ኼደንበታል በማለት ችግር ያለው የሌሊት አልባሳት ላይ ነው ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል ጽ/ቤት በበኩሉ ከተፈናቃዩ ቁጥር አንፃር ማስተናገድ ቢከብድም ተፈናቃዮቹን ለማገዝ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ አመልክቷል፣ በአማራ ክልል የተፈናቃዩ ቁጥር 2 ሚሊዮን 300 ሺህ መድረሱን ደግሞ የክልሉ መንግስት ዐስታውቋል። መንግሥት ሸኔ በሚለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ታጣቂ ከዚህ በፊት ወለጋ ውስጥ የ15 ዓመት ልጃቸው የተገደለባቸውና ባለቤታቸው በከባድ መሳሪያ ተመትተው የአካል ጉዳተኛ የሆነባቸው እናት ተፈናቅለው ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ ቢመጡም ርዳታ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የሚናገሩት።  ቀደም ባሉት ጊዚያት የተወሰነ ርዳታ ይደርሳቸው እንደነበር የነገሩን ሌላው ተፈናቃይ፣ የመኖሪያም ሆነ የምግብ እጥረቶች አሉብን ብለዋል።

ከ60 ዓመት በላይ ለሆናቸው 10 ያህል ተፈናቃዮች መንግስት ትናንትና በሐይቅ መጠለያ ጣቢያ እስከ 15 ኪሎ ስንዴ ስጥቶ እንደተመለሰ የተናገሩት የወለጋው ተፈናቃይ ሌሎቻችንን ግን ዞር ብሎያየን የለም ሲሉ ነው በምሬት ያስረዱት። በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ይመር በዞኑ ከ34 ሺህ በላይ ተፈናቃይ እንደሚኖር አመልክተው 8ሺህ የሚሆኑት በመጠለያ ይኖራሉ ብለዋል።

የተፈናቃዩ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ በተለይ የአልባሳት ችግሮች መኖራቸውንና መፍትኄም እተፈለገ እንደሆነ ገልጠዋል። ተፈናቃዮቹ በዋናነት ከኦሮሚያ፣ ከአፋር፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከደቡብና ከራሱ ከአማራ ክልሎች የተፈናቀሉ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን እንዳሉት ደግሞ በክልሉ ከ2 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ተፈናቃይ መኖሩንና በየወሩ 1 ሚሊዮን 300 ሺህ ኩንታል እህል እየቀረበ ነው ብለዋል። 70 ከመቶ የሚሆነውን የምግብ እህል መንግስት እያቀረበ ሲሆን፤ ቀሪውን ደግሞ የልማት ድርጅቶችና አጋር አካላት እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል። የአልሚ ምግብ እጥረቶች እንዳሉ ያመለከቱት አቶ እያሱ፣ የምግብ እህል በማድረስ በኩል የመቆራረጥ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙም ገልፀዋል። በአማራ ክልል ከ11 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የእለት ምግብ እርዳታ ፈላጊ መሆኑንም አቶ እያሱ አስረድተዋል። 

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ