1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የኦንላይን ዘለፋ እና ማሸማቀቅ ከፍተኛ መሆኑን ጥናት አመለከተ

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2016

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በሀሰት እና በተዛባ መረጃ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው፤በማህበራዊ ህይወታቸው፣ በቤተሰባቸው ፣በስራ አካባቢያቸው እና በሙያቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን ጥናቱ አመልክቷል ። አንዳንድ ሴቶች በበይነመረብ በተደረጉ ዘመቻዎች ምክንያት አካላዊ ጥቃት ወይም እንግልት እንደደረሰባቸው ለአጥኝዎቹ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4g9yD
በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች  በሀሰት እና በተዛባ መረጃ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው፤በማህበራዊ ህይወታቸው፣ በቤተሰባቸው ፣በስራ አካባቢያቸው እና በሙያቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን ጥናቱ አመልክቷል ።
በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በሀሰት እና በተዛባ መረጃ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው፤በማህበራዊ ህይወታቸው፣ በቤተሰባቸው ፣በስራ አካባቢያቸው እና በሙያቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን ጥናቱ አመልክቷል ። ምስል Antonio Guillen Fernández/PantherMedia/IMAGO

በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሰው የኦንላይን ዘለፋ እና ማሸማቀቅ ከፍተኛ መሆኑን ጥናት አመለከተ


የዘመኑ ዲጅታል ቴክኖሎጂ የወለዳቸው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሰው ልጆችን በማቀራረብ፣ በማዝናናት እና መረጃ በመስጠት የሚጠቅሙትን ያህል ግላዊነትን አደጋ ላይ በመጣል፣ የጥላቻ ንግግሮችን እና የተዛቡ እና የውሸት መረጃዎችን በማሰራጨትም ጉዳት ያደርሳሉ።በቅርቡ በኢትዮጵያ የተደረገ አንድ ጥናትም ሴቶች  የበለጠ የዚህ ችግር ሰለባ መሆናቸውን አመልክቷል።
መቀመጫውን ብሪታኒያ  ያደረገው ሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ሪዚሊንስ/Centre for Information Resilience / የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም  በቅርቡ ይፋ ያደረገው ይህ አዲስ ጥናት  በኢትዮጵያ  በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ሴቶች ላይ የሚሰነዘሩ አሸማቃቂ ፣ማስፈራሪያ የታከለበት እና ጾታዊ ማንነትን የሚያንቆሽሹ የጥላቻ ንግግሮች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል። 

ይህም  ሴቶችን ከማህበራዊ ተሳትፎዎች  እንዲነጠሉ ፣ሀሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ እና በበይነመረብም ይሁን ከበይነመረብ ውጭ ያላቸውን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ እየገደበ እንደሚገኝ ጥናቱ አመልክቷል። በኢትዮጵያ የትኛውም የማህበራዊ መገናኛ ገፅ ለሴቶች ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም የሚለው ጥናቱ፤  ፌስ ቡክ ቀዳሚ የጥቃት መድረክ መሆኑን ገልጿል። የፌስ ቡክ መልዕክቶች ጎጂ ናቸዉ-ጥናት

ጥናቱን መነሻ በማድረግ ያነጋገርናት የህክምና ባለሙያዋ ዶክተር ማህሌት ሽመልስ በጥናቱ ግኝቶች ትስማማለች። ችግሩ ትኩረት አግኝቶ መጠናቱ ጥሩ ጅምር መሆኑን የምትገልፀው  ዶክተር ማህሌት  ከህክምና ስራዋ በተጨማሪ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በምታቀርባቸው በሴቶች መብት ላይ ያተኮ ሀሳቦቿ እሷም የዚሁ ችግር ሰለቫ መሆኗን ታስረዳለች።

ዶክተር ማህሌት ሽመልስ ፤ የህክምና ባለሙያ እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስርዓተ ጾታ ላይ የምትሰራ
ዶክተር ማህሌት ሽመልስ ፤ የህክምና ባለሙያ እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስርዓተ ጾታ ላይ የምትሰራምስል privat

«ሶሻል ሚዲያ ላይ አንዳንድ የምሰራቸው «አክቲቪቲዎች » አሉ። የምሰራቸው ቪዲዮዎች አሉ።  ሰወችን ማስተማሪያ ሴቶች ምን ያህል መብት እንዳላቸው ብዙ ከባህላችን ጋር እንደ ኢትዮጵያዊ ከምንኖርበት እይታ ጋር የማይሄዱ በጣም ከባድ የሆኑ ሴቶችን የሚጨቁኑ ብዙ መስመሮች እንደምንከከተል ለማሳየት የምሰራቸው ቪዲዮዎች አሉ ።እና በነዚያ ቪዲዮዎች ላይ ከቤት ጀምሮ እስከ ሰራቦታ እስከ ሃይማኖት ተቋም ተቋማት ብዙ የማውቃቸው ሰዎች «ነጌቲብ» የሆኑ በጣም ክፉ የሆኑ መጥፎ «አቲቲዩድ» ያለቸው አስተያየቶች ይደርሱኛል። በተለይ ሶሻል ሚድያ ላይ ለየት የሚለው ነገር ምንድነው፤ ፊታችን አይታይም በድብቅ ነው የምንናገረው። በድብቅ ማን እንደሆነ ሳንታወቅ የምንሰጣቸው «ኮሜንቶች» በጣም አደገኛ ናቸው። ሰፈሬን ጠርቶ እስከ መግደል ድረስ ሚያስፈራሩ «ሜሴጆች» ይደርሱኛል።» ስትል ገልፃለች። 

ምፀት፣ ፌዝ እና ፆታ ላይ ያነጣጠሩ ዘለፋዎች

ቡድኑ ጥናቱን ለማካሄድ በኢትዮጵያ ውስጥ በሲቪል ማህበረሰብ እና በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን 14 ሴቶችን አነጋግሯል።  የጥላቻ ንግግሩን ኢላማ፣ አይነት እና ባህሪ ለመለየትም በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር)፣ በቴሌግራም እና በፌስቡክ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ እና በእንግሊዝኛ የተጋሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጽሁፎችን ይዘት ተንትኗል። በዚህም ጥናቱ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ምንነት በወንዶች አቻዎቻቸው ከሚደርሰው በደል እንዴት እንደሚለይም አሳይቷል። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ወንዶች ከአመለካከታቸው ወይም ከፖለቲካ አቋማቸው ጋር በተዛመደ የበይነመረብ ላይ ጥቃት ሲደርስባቸው፣ ሴቶች በሚያቀርቡት ሀሳብ ሳይሆን፤ በአካላዊ ማንነታቸው፣ በትዳር ሁኔታ እና በተጠረጠሩ ግንኙነቶች ላይ የተመረተ  ጥቃት ይደርስባቸዋል።

ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ሴቶች ብዙውን ጊዜ ፌዝ ወይም ምፀት እንዲሁም ክብረነክ የሆኑ አገላለጾች  ሰለቫ ናቸው።ጥናቱ እንደሚያሳየው ይህ ዓይነቱ  በደል በሂደት በማህበረሰቡ ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳድር እና ሴቶች ከማህበራዊ ህይወት እንዲወጡ እና በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲገለሉ ያደርጋል። ይህ አይነቱ ነቀፌታ እና ማሸማቀቅ እንደ እርሷ በስርዓተ ፆታ ጉዳዮች ላይ በሚሰሩ ሴቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም ቢሆን የሴቶች ሀሳብ እና እይታ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በጥሩ መልኩ እንደማይሰተናገድም  ዶክተር ማህሌት ታዝባለች። ለዚህም ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ ያለውን የቆየ አመለካከት ምክንያትነት ትጠቅሳለች። «የ«ጀንደር ኢሹ» ብቻ ሳይሆን ማንኛዉንም ርዕስ ይዛ አንዲት ሴት ሶሻል ሚዲያ ላይ  ስትወጣ እና አንድ ወንድ ሶሻልሚድያ  ሲወጣ ያለው  አቀባብል በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የተለየ ነው። ጥሩ የሆኑ ርዕሶች ለማውራት እንኳ የሚሰጡት «ኮመንቶች» ከመልኳ ጋር  ከሴት ማንነትዋ ጋር የተያያዘ እንጂ ብዙ ጊዜ የምትናገረውን ነገር ጋር ዋጋ በመስጠት  አይደለም። እንግዲህ ምን አልባት የትምህርት ደረጃቸውን ያለንበት ሶሳይቲ ካልቸራል ና religious  እንደምክንያት ብዬ እንደምክንያት ብዬ የማነሳቸው። ብዙ ጊዜ ለሴቶች  የሚሰጠው ቦታና ለወንዶች የምሰጠው ቦታ  በኛ መሀበረሰብ የተለያየ ነው። ያ ደግሞ ሶሻል ሚዲያ ላይ «ሪፊሌክት» ማድረጉ የማይቀር ነገር ነው ብዬ አስባለሁ።»ብላለች።

ሌላዋ ጥናቱን በተመለከተ ዶቼቬለ ያነጋገራት ወጣት ፅላተ ሰለሞን ነች።ፅላተ ነፃነት የተባለ በበይነመረብ የሚሰራጭ ፖድካስት አዘጋጅ ስትሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኮሚዴ ስራዎችን ለታዳሚያን ታቀርባለች። በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ንቁ ተሳታፊ  መሆኗን የምትገልፀው ፅላተ በስራዎቿ በእነዚህ ዲጅታል መድረኮች አሉታዊ አስተያየቶች ይደርሷታል። ነገር ግን  አስተያየቶቹ  ሀሳብ ላይ ያተኮሩ ሳይሆኑ በእርሷ አካላዊ ገፅታ ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን ትገልፃለች።«አንዳንድ ጊዜ የሚሰጡት «ፊድባክ»  ለሴቶች የተባሉ ርዕሶችን ስታነሽ ይህን ለማውራት ከሆነ  ፖድካስት ምን ያደርግላችኋል አቤት ገብታችሁ አታወሩትም ይላሉ።  ሌላኛው ኮሜዲ ላይ ስራ ጋር በተያያዘ እና ሴት ከመሆን ጋር በተያያዘ ብዙ ነገር ትሰሚያለሽ። ኮሜዲ ትንሽ «ኖርማል» ከምንናገረው ነገር ወጣ ያሉ ነገሮች «ኤክስፕረስ» ሊደረግበት  የሚችል ቦታ ነው። እና ሴት ሆነሽ ደግሞ «ሪስኪ» የሚባሉ ሃሳቦችን ካነሳሽ በሱ የሚደርስብሽ «ነጌቲቭ ፊድባክ»በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። አሁን እስከዛሬ ሶስት የተለያዩ ቪዲዮዎች ምናልባት ከኔ ጋር በተያያዘ ይኖራል። የመጀመሪያ እና የመጨረሻው ቪድዮ «አፒሪያንሴ» ምን እንደምመስል ተነግሮኛል።» በማለት ተናግራለች።

የነፃነት ፖድካስት ተባባሪ አዘጋጅ ፅዮን ብሩክም የዚሁ ገፈት ቀማሽ ናት። «ሶሻል ሚዲያ ላይ ሲያውቁሽ  ማንነትሽን በጣም የምያውቁሽ ስለሚመስላቸው «ኮሜንታቸው ፐርሰናል» ይሆናል ማለት ነው። እንዴት ይህን ታስቢያለሽ ፣ቤተሰቦች እንዴት ቢሳድጉሽ ነው።በማለት background agenda ስላላችሁን ነው የሚል አስተያየት ሁሉ ከማታውቂያቸው  ሰዎች ይደርስሻል።» ስትል ገልፃለች። 

ፅላተ ሰለሞን እና ፂዮን ብሪክ የነፃነት ፖድካስት አዘጋጆች
ፅላተ ሰለሞን እና ፂዮን ብሪክ የነፃነት ፖድካስት አዘጋጆች ምስል Tsilate Solomon

በአዕምሮ ጤና ላይ ተፅዕኖ 

የኦንላይን  ጥቃት እና ትንኮሳ በገሃዱ ዓለምም ተፅዕኖው ቀላል አይደለም። ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል ከ78% በላይ የሚሆኑት በይነመረብ ላይ በደል ካጋጠማቸው በኋላ የፍርሃት ወይም የጭንቀት ስሜት እንዳላቸው ተናግረዋል።
 አንዳንድ ሴቶች ራሳቸውን ለመጠበቅ ከኦንላይን ውይይቶች እና መድረኮች ይርቃሉ። ብዙዎች እንደ ስሜት ቀውስ፣ ድብርት እና ጭንቀት ያሉ ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች አጋጥሟቸዋል። የፅላተ ገጠመኝ ይህንን የሚረጋግጥ ይመስላል። «በቲክ ቶክ  ደግሞ  ከኮሜንት በላይ ሰዎች ስለ አንቺ መናገር ይችላሉ። ቪዲዮውን በማያያዝ  ስላንቺ የፈለጉትን መናገር ይችላሉ። በእሱን በመጠቀም ከባድ የሆነ የኢንተርኔት ጥቃት  ሊደርስበሽ ይችላል። እኔም «ኤክስፔሪየንስ» ያደረጉት እሱን ነው። በሰአቱ በጣም አስደንጋጭ ነው። ሰው ኦንላይን ብቻ ተናግሮ አያልፍም። እና ይሄንንም እንድትፈሪ ያስገድድሻል። ምክንያቱም ሁሉም ሰው ኢንተርኔት ላይ ብቻ ተናግሮ የሚተው አይመስልሽም። የምትሄጅባቸው ቦታዎች ያስጨንቁሻል። የምትውያቸው ሰዎች ያስጨንቁሻል።እና የራሱ የሆነ «ሶሻል አንዛይቲ»ይዞ ይመጣል። የሆነ ሰው ተናገረ ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን በብዛት ነውና አንቺ ራስሽ ልታምኚ ይቃጣሻል። እነዚህ ሰዎች  የሚሉት ነገር እውነት ይሆን እንዴ የሚል ያንች አካል ይኖራል። ከባድ የሆነ ጥርጣሬ በራስሽ  ምርጫዎችና አስተሳሰብ ላይ እንዲያድርብሽ ይገፋፋል።» ብላለች።

ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች  በውሸት እና በተዛባ መረጃ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው፤በማህበራዊ ህይወታቸው፣ ቤተሰባቸው እና የስራ አካባቢያቸው እንዲሁም በሙያቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን አጥኝዎቹ ገልፀዋል። አንዳንድ ሴቶች በበይነመረብ  በተደረጉ ዘመቻዎች ምክንያት አካላዊ ጥቃት ወይም እንግልት እንደደረሰባቸው ለአጥኝዎቹ ገልፀዋል።ከዚህ ባሻገር  ለእስር እና ለስደት የተዳረጉ ስለመኖራቸውም ጥናቱ ፍንጭ ሰጥቷል።ይህም የጥቃቱን የአሳሳቢነት ደረጃ አሳይቷል። ፅላተ እንደምትለው  ምንም እንኳ በችግሩ ባትሰበርም ይህ ጥቃት ከስራ እስከ መባረር አድርሷታል።ስለሆነም ይህ መሰሉ ሴቶችን ከማንኛውም ተሳትፎ ያርቃል የሚል ስጋት አላት። «በ ቲክ ቶክ፣ በቴሌግራም፣በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ላይ «አክቲቢ» ሆኑ ሴቶች የሚደርሳቸው «ኮሜንት»እና ማስፈራሪያዎች ምን እንደሚመስሉ አውቃለሁ። ያሉበትን አካባቢ የሚሄዱበትን አከባቢ ድረስ፤ የሚነዱትን መኪና ወይም የተሳፍሩበትን መኪና ፎቶ አንስተው እየላኩ አይቼሻለሁ እመጣልሻለሁ። የሚሉ ማስፈራሪያዎች  እንደሚደርስባቸው በቅርብ አውቃለሁ። እኔም ከዛሬ ነገ ወደዚህ እሄዳለሁ ብዬ እፈራለሁ። በፖድካስቱም  በኮሜዲውም የተነሳ።  እና አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ማንም ሰው ራሱን ማስቀመጥ ስለማይፈልግ የሆነ ዕድል  ከሴቶች ላይ ይቀማል።»በማለት የበይነመረብ ጥቃት ሴቶችን ከተለያዩ  ተሳትፎዎች እንደሚገታ ገልፃለች። እንደ ጥናቱ ኢትዮጵያ ውስጥ በሴቶች ላይ በበይነመረብ  የሚፈጸም ጥቃት  ተለምዷዊ ነገር  የማይታይ ነው። ሴቶች  ስለሚደርስባቸው በደል ሲናገሩ፣ ይህን ማለፍ ካልፈለጉ በቀላሉ ከማህበራዊ መገናኛ ዘዴ  መራቅ እንዳለባቸው ይነገራቸዋል ሲሉ አጥኝዎቹ ገልፀዋል።በኢትዮጵያ የሀሰተኛና ጥላቻ ንግግሮችን የቃኘው ጥናት

የብሄር ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት 

በበይነመረብ  ሴት ከመሆን ጋር ተያይዘው ከሚመጡት  ፆታ ላይ ካነጣጠሩ የሽሙጥ፣ የስላቅ እና የማንቋሸሽ አስተያየቶች  ባሻገር  እንደ ብሄር ማንነት  ወይም ሀይማኖት ካሉ ሌሎች የማንነት መለያ ባህሪያት ጋርም ስለሚያያዝ ጥቃቱ ድርብርብ እና የሚያስከትለው ጉዳትም የከፋ መሆኑን በጥናቱ ሰፍሯል።
በአማራ እና በኦሮሞ ብሄረሰብ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ሲነጻጸር  ከፍተኛ መሆኑን ተመራማሪዎች ጠቁመዋል።ይህም መረጃው በተሰበሰበበት ወቅት በጎርጎሪያኑ ነሀሴ 2023 ዓ/ም እና የካቲት 2024 ዓ/ም ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን አስከፊ ግጭት የሚያንፀባርቅ ነው ተብሏል። ለፖለቲካዊ ክስተቶች ምላሽ የሚሰጡ የጥላቻ ንግግሮች  ግጭት ውስጥ በተሳተፉ የተወሰኑ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚሰነዘሩ የጥላቻ ንግግሮች የበለጠ ለጠብ የሚጋብዝ  እና ግጭት ቀስቃሽ ቃላትን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተገንዝበዋል ።ከ80 በላይ ቋንቋዎች በሚነገሩባት ኢትዮጵያ  የማህበራዊ  መገናኛ ዘዴ ኩባንያዎች የሚሳደቡ ጽሁፎችን ለመከታተል የሚያስችል ግብአት እና የሰው ሃይል ስለሌላቸው ብዙዎች ሪፖርት ከተደረጉ በኋላ ልጥፎቹ  ሳይነሱ ለቀናት እንደሚቆዩም ጥናቱ አመልክቷል።

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መተግበሪያዎች
የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መተግበሪያዎችምስል Yui Mok/empics/picture alliance

የመፍትሄ ርምጃዎች

አካል ጉዳተኝነት፣ የብሄር ማንነት እና ጾታ ላይ አትኩሮ የተሰራ ቢሆንም ሴቶች ከሌሎች ማንነቶች በበለጠ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጥላቻ ንግግር ተጎጂ መሆናቸው ተገልጿል። ይህንን ችግር ለመፍታት ፅላተ እንደምትለው  የሌሎችን ግላዊ መረጃ አሳልፎ መስጠት የሚያመጣውን መዘዝ ማስተማር፣ ችግር ባለበት ፅሁፍ ወይም ቪዲዮ ላይ ሀሳብ በመስጠት እና በማጋራት ተሳትፎ አለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፃለች። ፖሊሲና መመሪያም ተገቢ መሆኑን ታስረዳለች። «በትክከለኛ ጥናት ተደግፎ ህጎች የሚወጡበት ነገር ቢኖር ከ«ሳይበር ቡሊንግ» ጋር ተያይዞ መነሳት የሚኖሩ ነገሮች ቢኖሩ ጥሩ ነው  እኛ ሀገር ውስጥ። ኢንፎርሜሽን  እንደፈለገ አንድ ሰው መናገር እንዳይችል እና ለማስፈራራት የሚመከሩ ሜሴጆች እንዲከላከሉ። እነዚህ ሰዎች ምንም እንደማይፈጠር ስለሚውቁ ነው ስማቸው ፎቶአቸው ባለበት ፕሮፋይል «ሜሴጅ» አድርገው የማይባሉ ነገሮችን የሚሉት እና እነዚህ ነገሮች «አቴሽን» ቢሰጣቸው ባይ ነኝ።»በማለት ገልፃለች። ዶክተር ማህሌት በበኩሏ በግለሰቦች፣በማህበረሰቡ እና በመንግስት ደረጃ መደረግ አለባቸው ያለቻቸውን መፍትሄዎች ጠቁማለች። «አሁን ያለንበት «ፓትርያርካል» ወይም ወንድ-ገዝ ማኅበረሰብ ምን ያህል የከፋ ነገሮች እያመጣ እንደሆነ እያየነው ነው። በሴቶችና በወንዶች እኩልነት ብቻ ሳይሆን በምንኖርባት የስራ ክፍሎች እና የህይወት ክፍሎች ውስጥ።» ካለች በኋላ ይህንን ለመለወጥ  ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ሁሉም የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ገልፃለች። እንደ ዶክተር ማህሌት አንድ የተለዬ ሀሳብ ሲነገርም ሆነ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲታይ ከመናደድ እና የሀሳቡን ባለቤት ለማሸማቀቅ ከመሞከር ይልቅ ሀሳቡን በጥሞና መመርመር  እና መከራከር አልያም  መተው የተሻለ ነው።
«ሐሳባቸውን እና ድምፃቸውን ለማጥፋት መሮጥ ይህ ትክክለኛ ከሆነ «ሲቪላይዝድ ሶሳይቲ»የሚጠበቅ አይደለም። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ማስተካከል አለብን። እንደ ሀገር ፖሊሲዎች በደንብ መሠራት አለባቸው።» በማለት ዶክተር ማህሌት ሽመልስ የመፍትሄ ሀሳቦችን ጠቁማለች። 

እንደ ጥናቱ በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ይህ መሰሉ በደል ተባብሶ የቀጠለው  ችግሩን  ለመቅረፍ የመፍትሄ እርምጃ ባለመወሰዱ ነው።ስለሆነም በተቋሙ ዘንድ ይህ ጥናት ለለውጥ ያግዛል የሚል ተስፋ አሳድሯል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ