1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 23 2015

ጀርመን የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በጦርነቱ ከፍተኛ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለገጠማቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረጉ ነው። በጀርመን የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩት እነዚህ ወገኖች ለተቸገረዉ ህዝብ አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ መንግሥታት ዘላቂ ሰላም በማስፈን ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4Qkxp
Äthiopien Mekele | Hilfssammlung für Kriegsopfer in Tigray
ምስል Million Haile Selassie/DW

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ

በትግራይ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተደረገው ጦርነት ያስከተለው ከባድ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በርካቶችን ለተረጂነት የዳረገ ሆንዋል። የክልሉ አስተዳደር ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በትግራይ የሚኖር ከአምስት ሚልዮን በላይ ህዝብ እርዳታ ፈላጊ ነው። ለዚህ ከፍተኛ ችግር ላይ ያለ ህዝብ የተለያዩ ሃገራት መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ተቋማት እያደረጉለት ካለው ድጋፍ በተጨማሪ፣ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችም በተለያየ መጠን የሚገለፅ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ። በትግራይ ያለውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል በማለም በቅርቡ በጀርመን የሚኖሩ በዜግነት ጀርመናውያን እና ኢትዮጵያውያን የትግራይ ተወላጆች በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። እነዚህ በፍራንክፈርት፣ ኮለን፣ ሙኒክ እና ሌሎች የጀርመን ከተሞች በተለያየ ሥራ ተሰማርተው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በጦርነቱ ቀጥታ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግር ለገጠማቸው በትግራይ ክልል ማርያም ሸዊቶ፣ እንዳባገሪማ እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ከ400 በላይ ዜጎች የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፣ በዚህ ድጋፍ እያንዳንዱ ተጎጂ ከሁለት ሺህ በላይ በጥሬ ገንዘብ እንዲያገኝ መደረጉን አስተባባሪዎች ነግረውናል።

ከጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በመምጣት የገንዘብ ድጋፍ ለተረጂ ቤተሰቦች ያስረከቡት በዜግነት ጀርመናዊ የሆኑት የትግራይ ተወላጅ አቶ ተወልደ ተስፋይ፣ በጦርነቱ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት የደረሳቸው የትግራይ አካባቢዎችን በመለየት፣ በጀርመን ካሉ የክልሉ ተወላጆች የተሰበሰበ ገንዘብ እጅግ በጣም ከፍተኛ ችግር ላይ ላሉ ቤተሰቦች መለገሱን ይናገራሉ። ትንሽም ቢሆን ማንኛውም ዓይነት እርዳታ ችግር ላይ ላለው የትግራይ ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው የሚገልፁት አቶ ተወልደ፥ ከእርዳታ ውጭ ህዝቡ ዘላቂ ሰላም አግኝቶ በሚኖርበት ሁኔታ ላይ በቀጣይነት መሥራት ይገባል ባይ ናቸው። 

Äthiopien Mekele | Hilfssammlung für Kriegsopfer in Tigray
ትግራይ ውስጥ በጦርነት ለተጎዱት ወገኖች የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ምስል Million Haile Selassie/DW

በትግራይ ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በተለያዩ ሃገራት በሚኖሩ ወገኖች እንዲሁም ሀገር በቀል ተቋማት ይከወናል። ማሕበር ሕውነት ደቂሰብ፣ በአማርኛ ትርጉሙ የሰው ልጆች ወንድማማችነት ማሕበር የተባለ ላለፉት 20 ዓመታት በሰብአዊ ተግባራት ላይ የቆየ ተቋም እንዲሁ በዛሬው ዕለት በመቐለ ለሚገኙ 570 ከፍተኛ ችግር ያለባቸው እናቶች ለእያንዳንዳቸው አንዳንድ ሺህ ብር ለግሷል። የማሕበሩ ቦርድ አባል አቶ ምዕራፍ ካሣ፣ «በትግራይ ያለው ማሕበራዊ ችግር ማቃለል ለዓለም አቀፍ ተቋማት ወይም መንግሥታት የሚተው ሥራ አይደለም፣ የሀገር ውስጥ ተቋማትም በዚህ ላይ ይሥሩ» የሚሉ ሲሆን፣ ድርጅታቸው ሴቶችን መርዳት አጠቃላይ ችግሩ በመፍታት ላይ ያለውን ሚና በመረዳት እናቶችን በመምረጥ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር