1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤንሻንጉል ጉሙዝ የትምህርት መሠረተ ልማትን መልሶ ለመገንባት በርካታ ገንዘብ ያስፈልጋል መባሉ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 12 2015

የት/ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል ያለመ ሕዝባዊ ንቅናቄ በክልል ደረጃ ትናንት በአሶሳ ተጀምሯል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በክልሉ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በነበረው ግጭት 196 ት/ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ተናግረዋል። 287 ት/ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን በማመልከት ጥገና የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4U8D3
Äthiopien | Benishangul Gumuz | Regionale Bildungskonferenz
ምስል Negasa Desalegn/DW

«ከሰባት ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል»

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተጎዱና የወድሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ በጥናት መረጋገጡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተናገሩ።  አቶ አሻድሊ ሐሰን ከዚህም ሌላ በክልሉ ከሚገኙት 679 ትምህርት ቤቶች 95 በመቶ የሚሆኑት የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው ብለዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የተናገሩት ትናንት በአሶሳ ውስጥ በተካሄደው የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል በተዘጋጀው ሕዝባዊ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ላይ ነው። በመርኃ ግብሩ ላይም የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተገኝተዋል።  

የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል ያለመ ሕዝባዊ ንቅናቄ በክልል ደረጃ ትናንት በአሶሳ ተጀምሯል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በክልሉ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በነበረው ግጭት 196 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን በመርኃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ 287 ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን በማመልከት ጥገና የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል። ይህም በክልሉ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ተጽኖ ማሳደሩንም አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ የወደሙ እና የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን በክልሉ መንግሥት አቅም በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሶ መገንባት እንደማይቻል ነው ያመለከቱት። 
የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማች ለማሻሻል በአሶሳ በተዘጋጀው ሕዝባዊ ንቅናቄ መርኃ ግብር ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፤ የትምህርት ጥራት አሁንም ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል። በሀገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች ለመማሪ ማስተማር ሂደት አስተማማኝ የሆነ አቅርቦት እንደሌላቸውም አመልክተዋል። የትምህርት ቤቶች ሰፊ የመሠረተ ልማት ችግሮች የሚፈቱት ማኅበረሰቡን ያማከለ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲኖር ነውም ብለዋል። በዓለም ተወዳዳሪ ሀገርና ትውልድ ለመፍጠር ትምህርት ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠው ነው ያሉት ሚኒስትሩ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማትን ማሻሻል እና የመምህራንን አቅም በማጎልት ጥራት ያለው ትምህርት ለማዳረስ  እየተሠራ እንደሚገኝ  ተናግረዋል።  
በአጠቃላይ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የፈተና አሰጣጥና ምዘናን ፍትሐዊ ማድረግ፣ የትምህርት ካሪኩለም ማሻሻል እና የትምህርት ፖሊሲን መቀየር ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች መካከል እንደሆኑም ተገልጿል። የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን እና የወደሙትን መልሶ ለመገንባት የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ባለሀብቶችና ልዩ ልዩ የግል ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል። ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ካሉት 50ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 86 በመቶው የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም  71 በመቶው በላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለውጤታማ የመማር ማስተማር ሂዴት አስፈላጊ መሠረተ ልማት የላቸውም።

Äthiopien | Benishangul Gumuz | Regionale Bildungskonferenz
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል ያለመው ሕዝባዊ ንቅናቄ ፤ በአሶሳ ምስል Negasa Desalegn/DW

ነጋሳ ደሳለኝ 

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር