1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ኦሮሚያ የጸጥታ ችግር፤ ረሃብና ወረርሽኝ

ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2016

ምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ ያጋጠመው ወረርሽኝ ለበርካቶች ሞት ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ነው። በዞኖቹ ወባ እና መሰል ወረርሽኞች በከፋው ደካማ የጤና አገልግሎት አሰጣጥና በመድኃኒት እጦት ችግሮች የተነሳ ሊታከሙ በሚችሉ በሽታዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው እያለፈ መሆኑንም የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

https://p.dw.com/p/4Xuzn
ፎቶ ከማኅደር፤ ነቀምት ከተማ
ምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ ያጋጠመው ወረርሽኝ ለበርካቶች ሞት ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ ነቀምት ከተማ

የቄለም እና ምዕራብ ወለጋ ነዋሪዎች አቤቱታ

ባለፉት አምስት ዓመታት በከፋው የጸጥታ ችግር ከተፈተኑ አካባቢዎች ዋነኛው በሆነው በምዕራብ ኦሮሚያ ኅብረተሰቡን ከፈተነው የጸጥታ ሁኔታ ባሻገር፤ የጸጥታ እጦቱ ውስብስብነት ያስከተለው የምርት ማነስ እና የህክምና አቅርቦት ችግር አስከፊ ፈተና መደቀኑ ይነገራል። በተለይም በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የከፋው የበሽታ ወረርሽኞች መስፋፋት አፋጣኝ እልባት የሚሻ ነው ሲሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ በአጽንኦት ያነሱታል፡፡የምዕራብ ኦሮሚያ ተፈናቃዮች የርዳታ ጥሪ ከቄለም ወለጋ ዞን ጋኦቄቤ ወረዳ ሀብሮ ቀበሌ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ነዋሪ በአካባቢው መሻሻል ያላሳየው የጸጥታው ችግር ማኅበረሰቡን ለአስከፊ ችግር ዳርጎታል ይላሉ። አስተያየት ሰጪ ነዋሪው በየመንደሩ ዕለት በዕለት የሰው ሞት መስማት የተለመደ ሆኗል ነው ያሉት። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ከፊሉ ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ሲሆን ከፊሉ በበሽታው ምክንያት ያልቃሉ ብለዋልም። በጸጥታ ችግሩ ያለፉትን አምስት ዓመታት አምርቶ በቀለብም እራስን መቻል የማይታሰብ ሆኖ ዘልቋልም ነው የተባለው።

ከምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ ለሊስቱ ሎጲ ቀበሌ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው፤ «አሁን እኛ ጋ ከፍተኛ የምግብ እጦት ይስተዋላል፡፡ ይህም መነሻው ድርቅ አጋጥሞን አሊያም በፋጣሪ ቁጣ ሳሆን ሰው በፈጠረው ግጭት ወጥቶ ማረስ አይደለም፤ ወጥቶ መግባቱ ፈተና ሆኖ በመዝለቁ ነው፡፡» በማለት አለ ያሉትን የጸጥታው ችግር ያስከተለውን የረሃብ እና የጤና አደጋ ዘርዝረዋል።ግጭትና ወባ በወለጋ አስተያየት ሰጪው ወባ፣ ጉንፋን መሰል ተላላፊ በሽታ እና ታይፎይድ ጎልቶ ከሚታዩ በሽታዎች የሚጠቀሱ ቢሆንም በውል በምርምር የተደረሰበት አለመሆኑንም ግን ያስገነዝባሉ። በሽታዎቹ ተላላፊ ቢሆኑም ክትባት እንኳ በአካባቢው እንደማይሰጥም አመልክተዋል።

በኦሮሚያ ጤና ቢሮ የኅብረተሰብ ወረርሽኝ መከላከል አስተባባሪ ምክትል የቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ከበበ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ፤ ቢሮዋቸው ስለችግሩ ጥልቀት የሚያውቅ መሆኑን ገልጸው ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል። በኦሮሚያ ክልል የጤና ተቋማት መጎዳትኃላፊው በወረርሽኙ ስለተያዙ ሰዎች ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበው በተለይም የወባ ወረርሽኝ በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ እንደሚከፋ በማመልከት፤ ከወረዳ ወረዳም የጉዳት መጠኑ እንደሚለያይም አስረድተዋል። ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ለአምስት ዓመታት የቀጠለው ግጭት እና የሰላም እጦቱ አሁንም ይህ ነው የሚባል እልባት ሳያገኝ ስለመቀጠሉም ይነገርለታል። 

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ