1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

ሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ የኢትዮጵያን 30 በመቶ ጭነት እንዲያስተናግድ ትፈልጋለች

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 2016

የበርበራ ወደብ የኢትዮጵያን 30 በመቶ ጭነት እንዲያስተናግድ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት አቅደዋል። ለዚህም የወደብ አጠቃቀም እና የጉምሩክ ሥርዓቶችን የተመለከተ ሥምምነት በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል መፈረም አለበት። ሥምምቱ በሚቀጥሉት 60 ቀናት ሊፈረም እንደሚችል የሶማሌላንድ የወደቦች አስተዳደር ባለሥልጣን ኃላፊ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4fOvj
አማሊ የተባለ ግዙፍ መርከብ በበርበራ ወደብ ቆሞ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ንብረት የሆነው ዲፒ ወርልድ የሚያስተዳድረው የበርበራ ወደብ ባለፉት ዓመታት በተደረገለት ከፍተኛ ማስፋፊያ ግዙፍ መርከቦች ማስተናገድ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ምስል Eshete Bekele/DW

ሶማሌላንድ የበርበራ ወደብ የኢትዮጵያን 30 በመቶ ጭነት እንዲያስተናግድ ትፈልጋለች

ከሐርጌይሳ ወደ በበርበራ በሚያመራው አውራ ጎዳና ግራ እና ቀኝ ጠርዝ ለጥንቃቄ የተበጀው ምልክት ቢጫ ቀለም ገና አልደበዘዘም፤ አልተሸራረፈም። በነጭ ቀለም የተሠመረው የመንገድ ማካፈያ ብዙ አልተጎዳም። በሐርጌይሳ ወይም በርበራ ከተሞች መግቢያ እና መውጪያ ካልሆነ በቀር ዋናው አውራ ጎዳና ገርገጭ አያደርግም።

በመንገዱ የሚመላለሱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ለጊዜው አነስተኛ ነው። በጥቂት ወራት ውስጥ ግን የኢትዮጵያን የወጪ እና ገቢ ጭነት የሚያመላልሱ ከባድ ተሽከርካሪዎች ዋንኛ መንገድ መሆኑ አይቀርም የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። 

ይኸ መንገድ እስከ አዲስ አበባ የሚዘልቀው የበርበራ የማጓጓዣ እና የመሠረተ-ልማት ኮሪደር አንድ አካል ነው። ከአዲስ አበባ እስከ በርበራ የሚዘልቀው መንገድ በአጠቃላይ 937 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። ከዚህ ውስጥ 696 ኪሎ ሜትር በኢትዮጵያ የተቀረው 241 ኪሎ ሜትር ደግሞ በሶማሌላንድ ይገኛል።

“እኛ ለኢትዮጵያ ምርጥ ኮሪደር አለን” የሚሉት የሶማሌላንድ የወደቦች አስተዳደር ባለሥልጣን ዳይሬክተር ሳዒድ ሐሰን አብዲላሒ በርበራ የተሻለ አማራጭ እንደሚሆን እምነት አድሮባቸዋል።

ሳዒድ ሐሰን “ከበርበራ እስከ ሞጆ እና ከጅቡቲ እስከ ሞጆ ያለው ርቀት ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን በእኛ አካባቢ መንገዱ ተራራማ አይደለም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከየመን ተጭኖ ለሶማሌላንድ ገበያ የተራገፈ ሽንኩርት በበርበራ ወደብ
መለስተኛ መርከቦች ለሶማሌላንድ ገበያ የጫኑትን ቀይ ሽንኩርት በበርበራ ወደብ ያራግፋሉ። ምስል Eshete Bekele/DW

የኮሪደሩ ዋነኛ የልብ ምት የበርበራ ወደብ ነው። ባለፈው ሣምንት ሐሙስ ከበርበራ ወደብ ስደርስ መለስተኛ ጀልባዎች ከየመን የተጫነ ሽንኩርት ለሶማሌላንድ ገበያ ያራግፋሉ። በቀይ ከረጢት የተሞላው ሽንኩርት ወደ ጭነት መኪና መጫን ጀምሯል።

ከአነስተኛዎቹ ጀልባዎች እልፍ ብሎ ሦስት ግዙፍ መርከቦች ይታያሉ። መርከቦቹ በጊኒ ቢሳዎ፣ ቶጎ እና ፓናማ የተመዘገቡ ናቸው። ከሁለቱ መርከቦች እህል ወደ ጭነት ተሽከርካሪዎች መራገፍ ጀምሯል።

ከበርበራ ወደብ በግ፣ ፍየል፣ የቀንድ ከብት እና ግመል ወደ ዓለም ገበያ በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ይጫናል። ስኳር፣ ሩዝ፣ የስንዴ ዱቄት እና ስንዴ እንዲሁም የማብሰያ ዘይትን የመሰሉ ሸቀጦች ደግሞ ይራገፋሉ።

የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባውን የርዳታ እህል የሚያጓጉዘው በበርበራ ወደብ በኩል ነው። በወደቡ ለኢትዮጵያ ገበያ የሚቀርቡ ተሽከርካሪዎችም እንደሚጓጓዙ የሶማሌላንድ የወደቦች አስተዳደር ባለሥልጣን ዳይሬክተር ሳዒድ ሐሰን አብዲላሒ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ዕቅዱ ግን ከዚያም የላቀ ነው።

“በአሁኑ ወቅት የወደብ አጠቃቀም ሥምምነት (transit agreement) እያዘጋጀን ነው” ያሉት ሳዒድ ሐሰን አብዲላሒ “አንዴ ሥምምነቱን ከተፈራረምን በመጀመሪያው ዓመት ከኢትዮጵያ ጭነት 30 በመቶውን እናስተናግዳለን” ሲሉ አስረድተዋል።

የሶማሌላንድ የወደቦች አስተዳደር ባለሥልጣን ዳይሬክተር ሳዒድ ሐሰን አብዲላሒ
የሶማሌላንድ የወደቦች አስተዳደር ባለሥልጣን ዳይሬክተር ሳዒድ ሐሰን አብዲላሒ አስፈላጊ ሥምምነቶች ሲጠናቀቁ የበርበራ ወደብ በመጀመሪያው ዓመት የኢትዮጵያን 30 በመቶ ጭነት ያስተናግዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሥምምነት ወደ ተግባር የሚያሸጋግረው የመጨረሻ ውል በተመሳሳይ በሁለት ወራት ገደማ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሥምምነት ወደ ተግባር የሚያሸጋግረው ምዕራፍ ሶማሌላንድ ለሦስት አስርት ዓመታት የሻተችውን ዕውቅና የሚያጎናጽፍ ነው።

እንደታቀደው ሁለቱ ወገኖች ተደራድረው የመጨረሻውን ሥምምነት ከተፈራረሙ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የባሕር ዳርቻዎች የባሕር ኃይል የጦር ሠፈር የምትመሠርትበትን ቦታ በኪራይ ታገኛለች።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ባለሥልጣናት ከሶማሊያ ኃይለኛ ተቃውሞ የገጠመው የመግባቢያ ሥምምነት ሲተገበር ኢትዮጵያ ለንግድ አገልግሎት የሚውል ወደብ ጭምር ታገኛለች ብለው ነበር።

የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ሳዓድ አሊ ሽሬ ግን የበርበራ ወደብ “የኢትዮጵያን ነጋዴዎች እና መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች እንዲጠቀሙበት ክፍት ይሆናል። ስለዚህ ሌላ ወደብ መገንባት አያስፈልግም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

ወደቡ የሚገኝባት በርበራ አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ከመቀራመታቸው በፊት ጀምሮ የንግድ ማዕከል የነበረች ነች። ለሶማሌ አርብቶ አደሮች የንግድ ትሥሥር ቁልፍ ሚና ተጫውታለች። ከበርበራ የመጀመሪያው መንገድ ወደ ሐረር የተገነባው በጎርጎሮሳዊው 1940 ነበር።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ንብረት የሆነው ዲፒ ወርልድ የሚያስተዳድረው የበርበራ ወደብ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ማስፋፊያ ተደርጎበታል። የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ሳዓድ አሊ ሽሬ “አካላዊውን መሠረተ-ልማት በተመለከተ ወደቡን ገንብተናል። አንድ ኪሎ ሜትር የሚሰፋ የመርከብ መቆሚያ፤ ኮንቴነሮች መጫን እና ማውረድ የሚችሉ ዘመናዊ ክሬኖች ያሉት ዓለም አቀፍ ወደብ አለን” ሲሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወነውን ሥራ ይዘረዝራሉ።

የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ሳዓድ አሊ ሽሬ
የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ሳዓድ አሊ ሽሬ የበርበራ ወደብ “የኢትዮጵያን ነጋዴዎች እና መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች እንዲጠቀሙበት ክፍት ይሆናል። ስለዚህ ሌላ ወደብ መገንባት አያስፈልግም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

“ከበርበራ ወደብ በድንበር እስከምትገኘው ውጫሌ ያለውን መንገድ ገንብተናል። ከዚህ በተጨማሪ በበርበራ ነጻ የኤኮኖሚ ዞኖች አሉን። የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች ጋኖች፣ ከነዳጅ ጫኝ መርከቦች ማራገፊያ አዘጋጅተናል” ያሉት የፋይናንስ ሚኒስትሩ በመሠረተ-ልማት ረገድ የበርበራ ኮሪደር “ከሞላ ጎደል” መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የበርበራ ወደብ በአሁኑ ወቅት ሦስት ግዙፍ የዕቃ መጫኛ እና ማውረጃ ክሬኖች አሉት። በዓመት 500 ሺሕ ኮንቴነሮች ማስተናገድ የሚችል 300 ሺሕ ሜትር ስኩዌር የሚሰፋ ቦታም ተዘጋጅቷል። የበርበራ ወደብ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት እንደተመኙት የኢትዮጵያን 30 በመቶ ጭነት እንንዲያስተናግድ ቀሪው ሥራ ሕጋዊ ሥርዓት መዘርጋት ነው።

ሳዓድ አሊ ሽሬ “በሁለቱ ሀገሮቻችን መካከል የወደብ አጠቃቀም ሥምምነት (transit agreement) ሊኖረን ይገባል። የጉምሩክ ሥርዓቶቻችንን ማገናኘት ወይም ማስተሳሰር ይኖርብናል” ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ  ሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ የመጓጓዣ ሥምምነትም ማበጀት አለባቸው። “ከሥርዓት አኳያ በሒደት ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ጉዳዮች አሉ” ሲሉ አስረድተዋል።

ከሐርጌይሳ ወደ በርበራ የሚወስደው መንገድ
የበርበራ ወደብ ከአዲስ አበባ 937 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛልምስል Eshete Bekele/DW

“ሕጋዊው ጉዳይ በመንግሥታት መካከል የሚፈረም ነው። ሥምምነቱ እየተጠናቀቀ ነው” የሚሉት የሶማሌላንድ የወደቦች አስተዳደር ባለሥልጣን ዳይሬክተር “በአንድ ወይም በሁለት ቀሪ ጉዳዮች ላይ ብቻ” ውይይት እየተደረገ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የሚደረገው ውይይት “ምን አልባት በመጪዎቹ 60 ቀናት ውስጥ” ሊጠናቀቅ እንደሚችል የጠቆሙት ሳዒድ ሐሰን አብዲላሒ “ከ60 ቀናት በኋላ ሥምምነቱን ተፈራርመን ኮሪደሩን መጠቀም እንጀምራለን” ሲሉ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።  

ከስድስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ እና ዲፒ ወርልድ ጋር በተፈራረመችው ሥምምነት በበርበራ ወደብ ልማት የ19 በመቶ ድርሻ ባለቤት ሆና የነበረ ቢሆንም በሽርክናው አልዘለቀችበትም። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አሁንም በበርበራ ወደብ ድርሻ እንዲኖረው ፍላጎት መኖሩን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ ከጥቂት ወራት በፊት ጥቆማ ሰጥተው ነበር።  

ወደቡ በዋናነት ለኢትዮጵያ የተዘጋጀ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ “ሌሎች ከሌላ አካባቢ መጥተው [የበርበራን] ወደብ ለማልማት ድርሻ ካላቸው፤ ኢትዮጵያ ለምንድ ድርሻ አይኖራትም?” የሚል ሐሳብ መኖሩን ተናግረው ነበር። ጉዳዩ ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ የጠቆሙት ዓለሙ ድርድር መኖሩን ገልጸው “ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው” ብለዋል።

ሶማሌላንድ እና ዲፒ ወርልድ ከበርበራ ወደብ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነጻ የኤኮኖሚ ቀጠና አበጅተዋል። ነጻ የንግድ ቀጠናው ከወደቡ ወደ ኢትዮጵያ በሚያመራው መንገድ ላይ የሚገኝ ነው። ግንባታው ሦስት ምዕራፎች እንደሚኖሩት የሶማሌላንድ የወደቦች አስተዳደር ባለሥልጣን ዳይሬክተር ሳዒድ ሐሰን አብዲላሒ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የበርበራ ወደብ
የበርበራ ወደብ በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ሜትር የሚሰፋ የመርከብ መቆሚያ እና ሦስት የዕቃ ማውረጃ እና መጫኛ ግዙፍ ክሬኖች አሉትምስል Eshete Bekele/DW

የመጀመሪያው ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ በደንበኞች መያዙን የገለጹት ኃላፊው “ተጨማሪ 8 ኪሎ ሜትር ስኩየር ሚሰፋ ነጻ የኤኮኖሚ ቀጠና” እንደሚገነባ ተናግረዋል። የበርበራ ኤኮኖሚ ዞን 300,000 ካሬ ጫማ የሚሰፋ የማብሰያ ዘይት ማሸጊያ ፋብሪካ ጭምር ይኖረዋል።

አይናቸውን በኢትዮጵያ ገበያ ላይ የጣሉት ሶማሌላንድ እና ዲፒ ወርልድ የበርበራ ኮሪደርን የበለጠ የማሳደግ ዕቅድ አላቸው። ወደቡ በዓለም የመርከቦች ምልልስ ቁልፍ ሚና ካለው ባብ’ል መንደብ አጠገብ መገኘቱ ደግሞ የበለጠ ዕድል ከፍቷል።

“እጅግ ግዙፍ የኮንቴይነር ተርሚናል ለመገንባት እየሞከርን ነው። ምን አልባት በሚቀጥለው ዓመት ሊጀመር ይችላል” ያሉት ሳዒድ ሐሰን አብዲላሒ ለበርበራ ተጨማሪ 600 ሜትር የሚሰፋ የመርከቦች መቆሚያ ለመገንባት እና ሰባት ግዙፍ የዕቃ መጫኛ እና ማውረጃ ለመጨመር ዕቅድ መኖሩን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የታቀደው ተግባራዊ ሲሆን “በአጠቃላይ የበርበራ ወደብ የመርከብ መቆሚያ 1 ሺሕ 650 ሜትር ይሆናል ማለት ነው” ያሉት ሳዒድ ሐሰን አብዲላሒ “በዚህም 2 ሚሊዮን ኮንቴይነሮች ማስተናገድ እንችላለን። ለኢትዮጵያ ትልቅ እና ጥሩ አማራጭ ይሆናል” በማለት ተናግረዋል።

የበርበራ ኮሪደር በዋናነት በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት በአፍሪካ ቀንድ ለሚገኙ ወደብ አልባ ሀገራት ጭምር ያገለግላል የሚል ተስፋ አላቸው። ኮሪደሩ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳን ከመሳሰሉ ሀገሮች ጋር ቢተሳሰር የሶማሌላንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ሳዓድ አሊ ሽሬ “ንግድ እና ጉዞ ይስፋፋል። የማጓጓዣ ወጪ ይቀንሳል” ሲሉ ላቅ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር