1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ሰው እንደሁ መረጃ ፈልፍሎ ማግኘቱ አይቀርም»

ዓርብ፣ ሰኔ 2 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ቲክ ቶክ እና ዩቲዩብ የመሳሰሉ የተመረጡ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከታገዱ እንሆ አራት ወር ሆናቸው። ረዥም ጊዜ ያስቆጠረውን እገዳ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ወጣቶች እንዴት እየተወጡት ነው? በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት አጠያይቀናል።

https://p.dw.com/p/4SMZd
Social Media Apps auf Smartphone
ምስል picture alliance / empics

«ሰው እንደሁ መረጃ ፈልፍሎ ማግኘቱ አይቀርም»

ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። ለአብነት ያህል ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ፈተና ጋር ተያይዞ ተማሪዎች እንዳይኮርጁ በሚል ወይም ከድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና ተያይዞ ከተነሳው አመፅ በኋላ የኢንተርኔት አገልግሎት በሀገሪቱ ታግዶ እንደነበር መጥቀስ ይቻላል። አሁንም ጠቅላላ የኢንተርኔት አገልግሎት ባይባልም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ቲክ ቶክ እና ዩቲዩብ የመሳሰሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ታግደዋል። ይህም ከአራት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የሆነ ነው።  መንግሥት እገዳ እና ምክንያቱን በይፋ ባይገልፅም የኢንተርኔት እንቅስቃሴዎችን የሚከታተለው ኔትብሎክስ ከአራት ወራት በፊት በትዊተር ገጹ ባሰራጨው አጭር መልእክት ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹ አገልግሎታቸው መታገዱን ማረጋገጡን አስታውቋል። ስሟ እንዳይገልፅ የጠየቀችን አንዲት በጅማ ከተማ የፎቶ ኮፒ ቤት ያላት ወጣት እንደገለፀችልን እገዳው በስራዋ ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሯል። « ስራው ላይ የመቀዝቀዝ ሁኔታ አለ። ከዚያም አልፎ እስከመዝጋት የደረሰ ሰው አለ» ትላለች በተለይ ለስራዋ ቴሌግራም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያብራራችልን ወጣት« ብዙ የኮንስትራክሽን ደንበኞች አሉን። ብዙ ጊዜ በቴሌግራም ዶክሜንት ይለዋወጣሉ እና የሚፈልጉትን ይዘው መጥተው እኛ ጋር የማሳተም ወይም የማስጠረዝ ሁኔታ አለ።»
በጥር ወር የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ ዉስጥ 6,4 ሚሊዮን ወይም ከሐገሪቱ ሕዝብ 5,1 በመቶው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይጠቀማል። በየዓመቱ ከ 230 የሚበልጡ ሀገራትን ጥናቶች እና ትንታኔዎች አሰባስቦ ይፋ የሚያደርገው ዳታ ሪፖርታል  ስለ ኢትዮጵያ የኢንተርኔት እና ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዲጂታል 2023 ባለው ትንታኔው አክሎ እንደፃፈው እንደ ግሪጎሪያኑ በ2023 መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ 20.86 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ነበሩ።
ይሁንና እጎአ ከ2016 ዓ ም አንስቶ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎች ድርጅቶች እንደመዘገቡት በሀገሪቱ ሰፊ ተቃውሞ እና ግጭት በሚፈጠርባቸው ጊዚያትና አካባቢዎች በተደጋጋሚ የኢንተርኔት መዘጋት ወይም እገዳዎች ይፈጸማሉ። አዲስ አበባ የሚኖረው ፍሬዘር የሀገር ውስጡ ነዋሪ አሁን ላይ ያለውን እገዳ በምን አይነት መንገድ እያለፈ እንደሆነ ገልፆልናል። « ሶሻል ሚዲያን በሀገሩ ኔትዎርክ ማግኘት አይቻልም። ስለዚህ ሰዎች VPN እየጫኑ ሰብረው እየገቡ ነው መረጃ እያገኙ እና እየተለዋወጡ ያሉት» 
ሌላው ያነጋገርነው ወጣት ናርዶስ ይባላል። እሱም ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀሙ እና መረጃ እያገኙ እንደሆነ ይናገራል። ይሁንና «መረጃ የማግኘት መብታችን እንደተነፈግን ነው»። ይላል። « በሌላ ዘዴዎችም ይሁን መረጃ ይደርሰናል። ሆኖም አብዛኛው ሰው ተደራሽነት የለውም። በጊዜው የሚፈልገውን መረጃ እንዳያገኝ መሰናክል ይሆነዋል። »

Data visualization Mobile Internet Africa - map price differences
ኢትዮጵያ ውስጥ በእጅ ስልክ ኢንተርኔት መጠቀም ውድ ነው

ፍሬዘርን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ መንግሥት ሆነ ብሎ ኢንተርኔትን ያግዳል የሚል እምነት አልነበራቸውም። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማት ካገኙ ስድስት ወር ሳይሞላቸው ኢንተርኔት በሀገሪቱ ተዘግቷል።  « አዲሱ መንግሥት ወደ ስልጣን ሲመጣ በፊት የነበረውን ሁኔታ እንደሚያስቆም ነበር ቃል የገባው። ግን አሁን ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ መረጃ ማግኘት ከባድ ነው። አንዳንድ ቦታ እንደውም ፍተሻ በሚያደርጉበት ሁኔታ ስልክ ሁላ ይፈትሻሉ። እና ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኘን ነገር ስልክ ላይ ሴቭ ተደርጎ ካገኙ ሰዎችን የማጉላለት ሁኔታ አለ። ነፃነት የሚባል ነገር በጠቅላላው የለም። ወጣቱ ግን ባለው አማራጭ ክፍተቱን ተጠቅሞ መረጃ ይለዋወጣል። » ይላል ፍሬዘር።

እንደሚታወሰው በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ ትግራይ ውስጥ ስልክን ጨምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት ለሁለት አመታት ገደማ ተቋርጦ ነበር። አሁንም ቢሆን በመላው ሀገሪቱ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከታገዱ አራት ወር ሆናቸው። የተጣለው እገዳ በአስቸኳይ እንዲነሳ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሶስት ወራት በፊት ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ባስተላለፈዉ  ጥሪ እገዳውን በፍጥነት እንዲያነሱና ሰዎች ራሳቸውን የመግለጽና መረጃ በመፈለግ እንዲሁም በማግኘት መብት ጣልቃ የመግባት ልምዳቸውን እንዲያቆሙ አሳስቧል። ይሁንና ከውጭ ሀገራትም ይሁን ከማህበረሰቡ ጉዳዩ ያን ያህል ትኩረት ሲሰጠው አይታይም። ለምን?

Illustration | VPN
ዋጋው ቢወደድም VPN መጠቀም ለኢትዮጵያ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ብቸኛው አማራጭ ሆኗል።ምስል Rafael Henrique/ZUMAPRESS/picture alliance

« መንግሥት የህዝቡን ስነ ልቦና ተረድቶታል። አንድ ነገር ይፈጠራል። የሆነ ወቅት ላይ ጩኸት ይበዛል። ከዛ ያ ነገር ይረሳል። እንደገና ሌላ አጀንዳ ይነሳል። ማህበረሰቡ በብዙ ነገሮች ተወጥሮ ነው ያለው። የኑሮ ውድነት አለ። ከፍተኛ የሆነ የሰላም እጦት አለ።» የሚለው ፍሬዘር «ሰው መረጃ ፈልፍሎ ከማግኘት አይቆጠብም። ስለዚህ ኢንተርኔት መዝጋቱ መፍትሔ ይሆናል ብዬ አላስብም። ይልቁንስ መንግሥት የቤት ስራውን ቢሰራ ጥሩ ነው ይላል»
በጅማ ከተማ የምትኖረው ወጣት ደግሞ ጉዳዩ ትኩረት ያላገኘው «ሰዎች መረጃውን በተለያዩ አማራጮች ማግኘት በመቻላቸዉ ሳይሆን ዝምታን በመምረጣቸው ነው» ትላለች።  « የእኛ ሰው የሚገጥመውን ማንኛውንም ነገር አሜን ብሎ እየተቀበለ መኖር ጀምሯል። እንደኛ እንደ ስራ ብሎ ለያዝነው ግን እጅግ ከባድ ነው።» ስለሆነም ዋጋው ቢወደድም VPN መጠቀም ለኢትዮጵያ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ብቸኛው አማራጭ ሆኗል። 


ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ