1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕወሓት ከሱዳን ጦር ጋ ወግኖ እየተዋጋ ነው መባሉን አስተባበለ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2016

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ኃይላት ከሱዳን ጦር ጋር ወግነው እየተዋጉ ነው በማለት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ያቀረበውን ክስ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትናንት ባወጣው መግለጫ አስተባበለ ።

https://p.dw.com/p/4facd
Äthiopien | Flagge Tigray People’s Liberation Front (TPLF
ምስል Million Haileyessus/DW

ሕወሓት ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላት (RSF) ምላሽ ሰጠ

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ኃይላት ከሱዳን ጦር ጋር ወግነው እየተዋጉ ነው በማለት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ያቀረበውን ክስ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትናንት ባወጣው መግለጫ አስተባበለ ። የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ክስን አጣጥሎ ያወገዘው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፦ ሕወሓት ላይ የቀረበው ክስ የሱዳንን ግጭት ዓለም አቀፋዊ መልክ ለማስያዝ ያለመ ብሎታል ።

ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላት በኩል የተሰነዘረውን ክስ ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትናንት ባወጣው መግለጫ፥ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይላት ወይም (RSF) የሕወሓት ታጣቂ ኃይላት ከሱዳን ጦር ሰራዊት ጋር ወግነው እየተዋጉ ነው በማለት ያቀረበውን ውንጀላ አስተባብሏል። የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ሐይሎች ውንጀላ በጥብቅ እንደሚያወግዝ የገለፀው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፥ ቡድኑ ይህን ያለውም በሱዳን ያለውን ጦርነት አለም አቀፋዊ መልክ ለማስያዝ እና አለማቀፍ ድጋፍ ለማግኘት አልሞ ነው ሲል ወቅሷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በመግለጫው ሕወሓት የፖለቲካ ፓርቲ ነው፣ ታጣቂ ክንፍ አልያም ሚሊሻ የለውም ያለ ሲሆን የትግራይ ሕዝብም ከሱዳን ጋር ረዥም እና ወንድሟዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ፥ በትግራዩ ጦርነት ወቅትም ቢሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ጦርነቱ ሸሽተው ሱዳን መግባታቸው በዛም ጥሩ አቀባበል እንደተደረገላቸው መግለጫው ጨምሮ አስቀምጧል።

ሱዳንን ያደቀቀው የርስ በርስ ጦርነት ቀጣናዊ እንዳይሆን አስግቷል
ሱዳንን ያደቀቀው የርስ በርስ ጦርነት ቀጣናዊ እንዳይሆን አስግቷልምስል ohamed Khidir/Xinhua/picture alliance

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሐይሎች ባለፈው እሁድ ባወጡት መግለጫ የህወሓት ሐይሎች ከሱዳን ጣር ሐይሎች ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ መሆኑ መረጃዎች እንዳላቸው አስታውቀው ነበር። ፈጥኖ ደራሽ ሐይሉ የሱዳን ጦር ቅጥረኛ ተዋጊዎች ከጎኑ እያሰለፈ ስለመሆኑ መግለፁ ይታወሳል። ይህን ያጣጣለው የትላንቱ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ማብራርያ በእርስበርስ ጦርነት የውጭ ሐይሎች ተሳትፎ ምንኛ አፍራሽ ሚና እንዳለው ከትግራይ ህዝብ በላይ የሚያውቀው የለም ያለ ሲሆን በየትኛውም ሁኔታ ትግራይ በሱዳኑ ግጭት እጅ የምታስገባበት ምክንያት የለም ብሏል።

ግዚያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ሁለቱ ወገኖች ጦርነት ከሚያባብሱ ንግግሮች እንዲቆጠቡና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱም ጠይቋል። ይህ መካሰስ ምን ያሳያል ብለን የጠየቅናቸው ፖለቲከኛ እና የሕግ ምሁሩ አቶ ተስፋዓለም በርሃ ፥ የሱዳኑን ግጭት ቀጠናዊ መልክ የያዘ መሆኑ ማሳያ ብለውታል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር