1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ላሊበላ የተሸከመችው የጦርነት ጠባሳ

ዓርብ፣ የካቲት 4 2014

ሁለት ጊዜ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ገብታ በነበረችው ላሊበላ የጦርነት ጠባሳዎች ይታያሉ። ነዋሪዎች እንደሚሉት የትግራይ ኃይሎች ግድያና አስገድዶ መድፈር ፈጽመዋል። የትግራይ ኃይሎች መቀመጫ አድርገውት የነበረና በድሮን ሳይመታ እንዳልቀረ በሚገመት ሆቴል ግድግዳ ላይ የተዋጊዎቹ ጽሁፎች እንዳሉ ናቸው። አንድ መዋዕለ-ሕጻናት የፋኖ ማረፊያ ሆኗል

https://p.dw.com/p/46szR
Äthiopien | Verwüstungen in Lalibela
ምስል AFP via Getty Images

ላሊበላ የተሸከመችው የጦርነት ጠባሳ

በላሊበላ ከተማ የሚገኘው የቤተ-ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በማለዳው ጮራ ሰላም ሰፍኖበት ይታያል። ባለፉት ወራት በዙሪያው በሆነው ሁሉ የተነካ አይመስልም። የዶይቼ ቬለዋ ማርየል ሙለር ቤተ-ጊዮርጊስን በቅጡ ማየት ከምትችልበት ቦታ በተገኘችበት አንድ ማለዳ በመስቀል ቅርጽ በተሰራው ቤተ-ክርስቲያን የጠዋቱ ቅዳሴ ማብቃቱ ነበር። ቤተ-ጊዮርጊስ በመካከለኛው ዘመን ከዓለት ተፈልፍለው ከተሠሩ አስራ አንድ የላሊበላ አብያተ-ክርስቲያናት አንዱ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተማዋ በመጀመሪያው ዙር ለአራት ወራት በሁለተኛው ደግሞ ለአንድ ሳምንት በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ስትቆይ አብያተ-ክርስቲያናቱ ከጥፋት የዳኑት በደብሩ ዋና አስተዳዳሪ አባ ጽጌ ሥላሴ መዝገቡ ሳይሆን አይቀርም።

"አንደኛው ቅርሱ ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንዳያደርሱ በአካባቢው የሚያስቀምጧቸውን ከባድ መሣሪያዎች እንዲያነሱ መለመን ነበረብኝ። ሌላው የማሕበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን እንዳይዘርፉ ወይም እንዳያወድሙ በየቀኑ እንለምን ነበር። ሰዎችን ገንዘብ ሲዘርፉ፣ ሲያስሩ እነሱን ለማስለቀቅም በየቀኑ እንገናኝ ነበር ማለት ይቻላል" ሲሉ ዋና አስተዳዳሪ አባ ጽጌ ሥላሴ መዝገቡ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ላሊበላ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በነበረችባቸው ጊዜያት ነዋሪዎቿ ለመሸሽ ተገደው ነበር። የከተማዋ ነዋሪ የሆኑ የዕድሜ ባለጸጋ "ብዙ ሰዉ ሸሽቶ ሔዷል። የቀረንውም በጭንቀት ላይ ነው ተወጥረን የነበረው" ሲሉ ያሳለፉትን ሁኔታ አስረድተዋል።

በዚያው በላሊበላ ነዋሪ የሆነች ወጣት "መሳሪያ አቀባብለውብን ነበር። በሁለተኛው ሲገቡ ደግሞ ሴት ደፈሩ፤ ሰው ደበደቡ፤ ሰው ገደሉ" ብላለች። "በከተማው ዘረፋ ነው ያደረጉት፤ ዘረፋ ነው፤ ሴቶችን መድፈር ነው፤ መደብደብ ሁሉ አለበት። ሆቴሎቹን ዘረፉ" የሚሉ ሌላ የላሊበላ ነዋሪ እንስት "ውኃ የለም መብራት የለም" ሲሉ በወቅቱ መሠረታዊ ግልጋሎቶች ተቋርጠው እንደነበር አስረድተዋል።

Äthiopien Lalibela | Orthodoxe unterirdische monolithische Kirche Bete Giyorgis
ቤተ-ጊዮርጊስ በመካከለኛው ዘመን ከዓለት ተፈልፍለው ከተሠሩ አስራ አንድ የላሊበላ አብያተ-ክርስቲያናት አንዱ ነው።ምስል picture alliance / Sergi Reboredo

በላሊበላ ከሚገኙ ከፍተኛ ቦታዎች በአንዱ ላይ የተገነባው ክሊፍ ኤጅ ሆቴል በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አንዱ ነው። የሆቴሉ የጥበቃ ሠራተኛ የነበሩት አቶ ቢሆነ ረታ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የተወሰኑ የትግራይ ኃይሎች ተዋጊዎች እንደ ዋና መሥሪያ ቤት ይገለገሉበት ነበር።

ታጣቂዎቹ ላሊበላን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት በሆቴሉ ግድግዳዎች ላይ መልዕክት ጽፈዋል። "ወደ ሀገረ ትግራይ እንኳን ደህና መጡ" የሚለው በግድግዳው ከተጻፉት መካከል ይገኝበታል። "ትግራዋይ እንጂ ኢትዮጵያ አይደለሁም" የሚል ሌላ ጽሁፍም ይታያል።

አቶ ቢሆን ረታ "እነሱ እዚህ ስብሰባ እያካሔዱ ለጦርነት ሲዘጋጁ እዚህ ተመቱ። ያን ጊዜ ቤቱ ወደመ። [እኛን] ውጡ አሉን ወጣን። እዚህ ብንኖር አብረን እንሞት ነበር" በማለት በሆቴሉ የሆነውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ሆቴሉ የተመታው በድሮን ሳይሆን አይቀርም። ፓክስ የተባለው የኔዘርላንድስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባለሙያዎች በሆቴሉ የሚታዩት ስብርባሪዎች በቱርክ ሰራሽ ድሮን ላይ የሚገጠሙ የጦር መሣሪያዎች መሆናቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ቱርክ ድሮኖች ለኢትዮጵያ ሳትሸጥ አትቀርም በሚል ስትተች ቆይታለች። በኢትዮጵያው ጦርነት ለበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሞት ድሮኖች ተጠያቂ ይደረጋሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች እንደሚሉት በጦርነቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች አሰቃቂ ድርጊቶች ፈጽመዋል።

DW Premium Thumbnail | Äthiopien | Tigray Konflikt
የፋኖ ታጣቂ ቡድን የህወሓት ታማኝ ኃይሎች በላሊበላ የመጀመሪያውን ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በርካታ አዳዲስ ምልምሎች በአባልነት መዝግቧል። ምስል Mariel Müller/DW

በላሊበላ ከተማ ከሚገኙ መዋዕለ-ሕጻናት አንዱ በአሁኑ ወቅት የፋኖ ተዋጊዎች ጊዜያዊ የጦር ሰፈር ሆኖ ያገለግላል። የፋኖ ታጣቂ ቡድን የህወሓት ታማኝ ኃይሎች በላሊበላ የመጀመሪያውን ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በርካታ አዳዲስ ምልምሎች በአባልነት መዝግቧል። ከምልምሎቹ መካከል ሴቶች ጭምር ይገኙበታል።

ከምልምሎቹ አንዱ የሆነችው ሐይማኖት ታደሰ "የወንድምህ ቁስል አለ። ከዚያ በተጨማሪ የአክስቴ ባል ቢሆንም ያሳደገኝ እሱ እስከሆነ ድረስ የእሱ ሞት አለ። እንደ እህቴ የማያት የተደፈረችው ጓደኛዬ አለች። ምንም በማታውቅበት ዕድሜዋ ማለት ነው። ባገኛቸው እኔ ሕይወቴ እስክታልፍ ድረስ ነበር ከእነሱ ጋ የምታገለው" ስትል ፋኖን የተቀላቀለችበትን ምክንያት ለዶይቼ ቬለ አስረድታለች።

ሐይማኖትን ጨምሮ በላሊበላ ከተማ በሚገኘው መዋዕለ-ሕጻናት ካሉት የፋኖ ተዋጊዎች 50ዎቹ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የሚዘምቱ ናቸው። ተዋጊዎቹ ህወሓት ዳግም ጥቃት ቢፈጽም ሁለቱ ክልሎች የሚዋሰኑበትን አካባቢ መከላከል እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።

ማርየል ሙለር/እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ