1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሩሲያ መዋጋት እንፈልጋለን ያሉ ኢትዮጵያውያን

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 11 2014

ዩክሬን ውስጥ ጦርነት ለገጠመችው ሩሲያ መዋጋት እንፈልጋለን ያሉ ኢትዮጵያውያን ለምዝገባ ዛሬም አዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ፊት ለፊት እንደተሰለፉ ነው። ዶይቼ ቬለ ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ በስፍራው የተሰለፉትን ኢትዮጵያውያን አነጋግሯቸው ያገኘው ምላሽም ይህንኑን ያረጋግጣል።

https://p.dw.com/p/4A6lw
Äthiopien Addis Abeba | Schlange vor der Russischen Botschaft
ምስል Seyoum Getu/DW

«እነሱ ይዘው የመጡትን ማስረጃ ምንነት ዐላውቅም»

ዩክሬን ውስጥ ጦርነት ለገጠመችው ሩሲያ መዋጋት እንፈልጋለን ያሉ ኢትዮጵያውያን ለምዝገባ ዛሬም አዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ፊት ለፊት እንደተሰለፉ ነው። ዶይቼ ቬለ ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ በስፍራው የተሰለፉትን ኢትዮጵያውያን አነጋግሯቸው ያገኘው ምላሽም ይህንኑን ያረጋግጣል። ትናት ሰኞ በሰፊው በዚህ ስፍራ ተሰልፈው ለመመዝገብ ሲጋፉ የዋሉት ኢትዮጵያውያኑ ዛሬ ማክሰኞም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለምዝገባ የሚውል ነው የተባለውን ሰነዶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል። ይሁንና አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የአዲስ አበባ የሩሲያ ኤምባሲ ባለስልጣናት ለሩሲያ የሚዋጉ ሰራዊት ከኢትዮጵያ እየመለመሉ አለመሆኑን ነው የሚገልጹት። ሩስያ ለሚጓዙ ግን እንደ ሁልጊዜው ቪዛ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል። 

ሰሞኑን የተጀመረው አዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ፊት ለፊት የሚሰለፉ ወጣቶች ቁጥር ዛሬ ማለዳውን በስፍራው ተገኝተን እንዳስተዋልነውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሩሲያን ጦር ለመቀላቀል ያላቸውን ፍላጎት በመግለጽ ሰነዶቻቸውን ለኢምባሲው ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ስሙን ለመግለጽ ፈቃደኛ ባሆንም ትናንት ማስረጃዎቹን አሟልቶ እንዲመጣ በኤምባሲው ተነግሮት ውትድርና ውስጥ ያለፈበትን ማስረጃውን አሟልቶ በመምጣቱ መመዝገቡን ከሰልፉ ውስጥ ዶይቼ ቬለ ያነጋገረው አንድ ወጣት ተናግሯል፡፡ 

Äthiopien Addis Abeba | Schlange vor der Russischen Botschaft
ምስል Seyoum Getu/DW

ጓደኛውን ጨምሮ ትናንት በርካታ ሰዎች መመዝገባቸውን የሚገልጸው ይህ ወጣት አስቀድሞ መረጃውን ያገኘው ቀጥታ ከኤምባሲው ሳይሆን በተዘዋዋሪ ከሰዎች መሆኑን ያስረዳል፡፡ ኤምባሲው ሲመጡ ግን አስፈላጊው መስፈርት ተነግሯቸው እየተመዘገቡ እንደሚመለሱም በማስረዳት፡፡ ሌላው ለመመዝገቡ ወደ ኤምባሲው አቅንቶ ሳይሳካለት እንደቀረ የሚናገረው የአንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሶስተኛ ዓመት የአካውንቲንግ ተማሪ ወጣት አብረሃም ይበልጣት ከዚህ ቀደም በውትድርና ሙያ የሰለጠነበት ማስረጃ ስለሌለው ምዝገባው ሳይሳካለት በመቅረቱ እንደሚቆጨው ነው የሚናገረው፡፡ 

ጉዳዩን አስመልክቶ አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሩሲያ ኤምባሲ ፕሬስ አታቼ ማሪያ ቼርኑክህና ነገሩ አሉባልታ ነው በማለት አስተባብለው ምላሽ ሰጥተዋል። 
«ዩክሬን ላይ ኦፕሬሽን ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ አበረታች መልእክቶችን ከኢትዮጵያውያን ስንቀበል ነበር። ባለፈው አንድ ወር በተለይም ከአንድ ሳምንት ወዲህ ደግሞ በርካቶች ወደ ኤምባሲያችንም ጭምር መጥተው ድጋፋቸውን እየገለጡ ነው። ለወታደራዊ ዘመቻ እተመዘገቡ ነው ሚለው ወሬ ግን አሉባልታ ብቻ ነው። ኤምባሲያችን በጦርነት የሚሳተፉ ሰራዊት የሚመለምል ኤጄንሲ አይደለም። ይህ የኤምባሲያችን ተልእኮም አይደለም፡፡ ኤምባሲያችን ይህን አያደርግም። እንደጋዜጠኛ እንድትረዳ የምፈልገውም ነገሩ አሉባልታ ነው ኤምባሲያችን መሰል ቅጥር አይፈጽምም።»

Äthiopien Addis Abeba | Schlange vor der Russischen Botschaft
ምስል Seyoum Getu/DW

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ዶይቼ ቬለ የወታደራዊ ስልጠና ሰነድ ይዘው ለኤምባሲው የሚያቀርቡትን ኢትዮጵያውን በስፍራው ተመልክቶ ማነጋገሩን ስናነሳላቸውም ይህን ብለዋል።
«እነሱ ይዘው የመጡትን ማስረጃ ምንነት ዐላውቅም። እኛ የምናውቀው እንደ ማንኛውም ኤምባሲ ወይም ቆንስላ አገልግሎት ፈላጊ ሰዎች ሲመጡ እያስተናገድናቸው ነው፡፡ እኛ የምንቀበላቸውም መታወቂያ እና ሌሎች ለጉዞ አስፈላጊ የሆኑትን ብቻ ነው። እነዚህ የምትለኝን ዶክመንት ይዘው የሚመጡ ካሉ ያው ካላቸው ፍላጎት ብቻ ነው ሊሆን ሚችለው። እውነት አይደለም። እንደ ቬይና ኮንቬንሽን ይህ የሚከለከል ስለሆነ እኛ ሕግ አንጥስም።»

ሩሲያ እና ኢትዮጵያ የዘመናት የዲፕሎማሲ እና የወንድማማችነተ ግንኙነት እንዳላቸው የሚገልጹት ማሪያ፤ ከባድ ባሉት በዚህ ጊዜ «ከሩሲያ ጎን ቁመው መርዳት የሚፈልጉትን በተለይም በውጊያው ሊረዱ የሚፈልጉትን እንዴት አድርገን እንደምንረዳቸው አላውቅም» ነው ያሉት። ወደ ሩሲያ ለመጓዝ ለሚሹ ግን እንደ ሁልጊዜውም የቪዛ እና ሌሎች አገልግሎቶች እየተሰጠ ነው በማለት መልሰዋል። ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ወዲህ ግን ምዕራባውያን አገራት ሩሲያ በተለይም ከመካከለኛው ምስራቅ ተዋጊዎችን ትመለምላለች በማለት ደጋግመው ያነሱታል።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ